ቀጥታ፡

እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ልዩ ቦታ ትሰጠዋለች - ፕሬዝዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015 (ኢዜአ):- እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ልዩ ቦታ እንደምትሰጠው የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ ገለጹ።

በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ የሹመት ደብዳቤያቸውን ዛሬ ለፕሬዝዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ አቅርበዋል።

አምባሳደር ተስፋዬ ከፕሬዝዳንት ጋር በነበራቸው ውይይት በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ያለውን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እና በተለያዩ መስኮች ለማስፋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ የግድቡ ግንባታ አላማ ለልማት ፍላጎት ምላሽ መስጠት መሆኑንና ኢትዮጵያ ለፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ ተገዢ እንደሆነች ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የተጀመረው የሕዳሴ ግድብ ሶስትዮሽ ድርድር ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ እንደሚያስገኝ እምነት እንዳላት ተናግረዋል።

የአረብ ሊግ በየጊዜው የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚያወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

አምባሳደር ተስፋዬ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባለው የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ ላይ ያላትን ሚና አስመልክቶ ምክክር አድርገዋል።

የእስራኤል ፕሬዝዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ታሪካዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በእስራኤል ልዩ ቦታ እንዳለው ገልጸዋል።

አምባሳደሩ በቆይታቸው የአገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አምባሳደሩ በእስራኤል ቆይታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም