በኢትዮጵያ ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦችን ለማረቅ የተሳሳቱ ትርክቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት ይገባል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦችን ለማረቅ የተሳሳቱ ትርክቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት ይገባል - ምሁራን
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦችን ለማረቅ የተሳሰቱ ትርክቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ፡፡
ጽንፈኝነት የዜጎችን አብሮነት በማወክ በአገር ሰላምና ድህንነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚፈጥር ሲሆን፤ ይህንን አካሄድ ማስተካከል ደግሞ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ትብበር ይጠይቃል፡፡
በተለይ ምሁራን ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለችግሩ መፍትሄ ከማመላከት ባሻገር ለዜጎች አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት መምህርት ዶክተር አጋረደች ጀማነህ፤ የጽንፈኝነት እሳቤ በመገናኛ ብዙሃን ጭምር እንደሚንጸባረቅ ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን በኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸው ይህንን እሳቤ በመታገል ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲጎለብት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አበበ በበኩላቸው፤በሁሉም የኢትዮጵያ ጫፎች የተዘራው የተሳሳተና ከፋፋይ ትርክት ችግሮችን በምክንያታዊነት የመፍታት ባህል ላይ አሉታዊ ጫና ሲፈጥሩ ይስተዋላል ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖራት የሚፈልጉ ሃይሎች በሃይማኖት ሽፋን ጭምር የጽንፈኝነት እሳቤን እንደሚያራምዱ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ናቸው፡፡
በሁሉም ሃይማኖት አስተምሮ ፍቅርና ሰላም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ አብሮነትና ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም በኃላፊነት ሊሰራ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ፤ በኢትዮጵያ ጽንፈኝነትን ለማስወገድ ሀገራዊ አንድነትን ከብሔራዊ ማንነት ጋር አቻችሎ መሄድ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በፖለቲካ አካሄድ ውስጥ የአገር ህልውና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባም እንዲሁ ፡፡
ኢትዮጵያ እንድትረጋጋና ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንድትገባ በሁሉም አካላት ዘንድ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች መወገድ እንዳለባቸው የሚገልጹት ምሁራኑ፤ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት መፍታት ብቸኛው መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሁሉም አካላት በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በውይይትና ለመፍታት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡