የቴሌኮምዩኒኬሽን ኩባንያው ኢቲሳላት በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

335

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ):-የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቴሌኮምዩኒኬሽን ኩባንያ ኢቲሳላት በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከኢቲሳላት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃተም ዶዊዳር ጋር በበይነ መረብ ተወያይተዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው ኩባንያው በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ የመሰማራት እንዲሁም በዘርፉ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለመመልከት ከኢትዮጵያ መንግስትና የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች በቀጣዮቹ ሳምንታት በኢትዮጵያ ተገናኝተው ውይይታቸውን ለመቀጠል መስማማታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቴሌኮምዩኒኬሽን ኩባንያ ኢቲሳላት የተቋቋመው እ.አ.አ በ1976 ነው።

ኩባንያው በአፍሪካ፣ እስያና መካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ 16 አገራት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞች እንዳሉት መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያ ለሶስተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ተቋም ፈቃድ ለመስጠት በሰኔ 2015 ዓ.ም ጨረታ እንደሚወጣ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ከቀናት በፊት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም