ቀጥታ፡

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ   የቦንድ ግዥ ለማከናወን በባህር ዳር ከተማ የሴት  አደረጃጀቶች ንቅናቄ ተጀመረ

ባህር ዳር  ግንቦት 15 /2015 (ኢዜአ)፡-  ለታላቁ የህዳሴ ግድብ  ድጋፍ የሚውል የቦንድ ግዥ ለማከናወን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር  የሴት አደረጃጀቶች የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ተካሄደ። 

በአማራ ክልል  ደረጃ  ባለፉት ዘጠኝ  ወራት 16 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በቦንድ ግዥ መሰብሰቡን የክልሉ  የግድቡ  ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
 

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር  የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሁሉአገርሽ አቻሜለህ እንዳሉት፤  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለፍፃሜ እንዲበቃ የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል።

እስከ ግንቦት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በሚቆየው የቦንድ ግዥ ንቅናቄ የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶችን በማሳተፍ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥ ለመሰብሰብ ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።    

በማስጀመሪያ መድረኩም ከ7 ሺህ 700 ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈፀሙን ጠቅሰው፤ ግድቡ የሴቶችን ችግር የሚፈታ በመሆኑ ሴቶች ግንባር ቀደም ሆነው እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

በቦንድ ግዥ ንቅናቄውም የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች በመጠቀም ከ10 ሺህ የሚበልጡ ሴቶች እንደ አቅማቸው በቦንድ ግዥው እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል።  


 

የአማራ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተናኘ አበበ በበኩላቸው፤  መላ ህዝቡ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብና በጉልበት አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በወጣቶች፣ ሴቶችና አርሶ አደሮች የተፈጠረው ንቅናቄ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ግድቡ ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋትና እድገት ያለው አስተዋፅኦ ለህዝቡ በማስገንዘብ ሁሉም በአቅሙ ልክ ቦንድ እንዲገዛ የተጠናከረ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ዘንድሮ በክልል ደረጃ ለመሰብሰብ ከታቀደው 20 ሚሊዮን ብር ውስጥ ባለፉት 9 ወራት 16 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ  በቦንድ ግዥ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

በቀሪ ወራትም እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ሰፊ የንቅናቄ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በመላ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ  የተጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለፍፃሜ እንዲበቃ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል ያሉት ደግሞ በቦንድ ግዥ የተሳተፉት ወይዘሮ ውቢት ተፈሪ ናቸው።

የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የገጠር ሴቶች  በጭስ ምክንያት ከሚደርስባቸው ችግር  እንዲላቀቁ ብሎም  ከድህነት ለመውጣት ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ የ5 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰው፤  ዛሬም የ500 ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አዲሴ አትንኩት ''ቀደም ሲል እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ለህዳሴው ግድብ ቦንድ በመግዛት የዜግነት ድርሻችንን ተወጥተናል'' ብለዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገር ህልውና ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሁላችንም ከህፃን እስከአዋቂ ተረባርበን ስራውን ለማጠናቀቅ ጥረት እያደረግን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን በቦንድ ግዥና በስጦታ 13 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተሰብስቦ ድጋፍ መደረጉን ከማስተባበሪያ ምክር ቤቱ  ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም