የአፍሪካ ሪጂን 4 ጎልፍ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት አዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ):-  የአፍሪካ ሪጂን 4 ጎልፍ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ጎልፍ ክለብ አሶሴሽን ገለጸ። 

አሶሴሽኑ ውድድሩን ለማካሄድ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ጎልፍ ክለብ አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ተሾመ ሞሲሳ የሻምፒዮናው ውድድር ከግንቦት 28 እስከ  ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ ይካሄዳል ብለዋል።

በውድድሩ  ከአፍሪካ ሪጅን 4 አባል አገራት መካከል አምስት የውጭ አገራት በውድድሩ ለመሳተፍ ማረጋገጫ መስጠታቸውን ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት ውድድሩን ለማዘጋጀት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም።

በውድድሩ ኢትዮጵያም ተካፋይ እንደመሆኗ ስፖርተኞች ተመርጠው ዝግጅት እያደረጉ ነው ብለዋል።

ውድድሩ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለአገር ገጽታ ግንባታና የእርስ በእርስ ግንኙነት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የገለፁት።

የጎልፍ ስፖርት በኢትዮጵያ የተጀመረው በቀዳማዊ ሃይለሥላሴ ዘመን ቢሆንም ስፖርቱ በሚፈለገው ደረጃ ሳያድግ ቆይቷል።  

ያም ሆኖ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ ስፖርቱ የተሻለ የሚባል እንቅስቃሴ እየታየበት የመጣ ሲሆን ኢትዮጵያ 2008 ዓ.ም በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነ የምስራቅ አፍሪካ ጎልፍ ውድድር አዘጋጅታ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም