ዓረብ ሊግ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ ያሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ "ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት' ነው - ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ - ኢዜአ አማርኛ
ዓረብ ሊግ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ ያሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ "ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት' ነው - ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015 (ኢዜአ)፡- ዓረብ ሊግ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተመለከተ ያሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ "ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት' ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካና እስያ ጥናት ማዕከል መምህር ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት የዓረብ ሊግ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበለው መግለጹ ይታወሳል።
የውሳኔ ኃሳቡ ግድቡን በተመለከተ ግብጽ የያዘችውን የተሳሳተ አቋም የሚያንጸባርቅ መሆኑንም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ የሚያሳየው።
በተለይም ግድቡን በተመለከተ የሚነሱ ጉዳዮች በሠላማዊ መንገድ በአፍሪካ ኅብረትና በአባል አገራት ጥረት ለመፍታት የሚደረገውን ሥራ የሚያንኳስስ መሆኑን ኢትዮጵያ ገልጻለች።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካና እስያ ጥናት ማዕከል መምህር የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ተፈራም የዓረብ ሊግ የውሳኔ ኃሳብ 'ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት' ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ የምታካሂደው የውሃ ሙሌት ያለ ሥምምነት በማስመሰል ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ ከመሙላት መቆጠብ አለባት በማለት የጠቀሱት ጉዳይ ጣልቃ ገብነትን የሚያረጋገጥ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በተጨማሪም የሱዳንና የግብጽ የውሃ ደኅንነት ጉዳይ የመላው የአረብ የውኃ ደኅንነት ጉዳይ በማድረግ ያሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ የአንድን ወገን በተለይም የግብጽን የቆየ ፍላጎት የማስቀጠል አካሄድ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም ይህ አድሏዊ የውሳኔ ሃሳብ ተቀባይነት የሌለውና በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የጋራ መፍትሄና መተማመን ለማፈላለግ የሚደረገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚጎትት መሆኑን ነው ያስረዱት።
የአረብ ሊግ ያሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ የአረብ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት እንዲሁም የወደፊትን ግንኙነት ከግምት ያላስገባ ለአንድ ወገን ያደላ የውሳኔ ኃሳብ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሊጉ ከዚህ ቀደም ከያዘው አቋም የተለየ ነው ማለት አይቻልም ያሉት ዶክተር ሳሙኤል ከእንዲህ አይነት አድሏዊ አቋም በመውጣት ለተፋሰሱ አገራት የሚጠቅም ውሳኔ ማሳለፍ እንዳለበት ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።
ግድቡን በተመለከተ የሚነሱ አለመግባባቶችን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የደረሱበትን የመርሆዎች ሥምምነት ማዕቀፍ መፍትሄ ማፈላለጉ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ፍትኃዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ ማክበሯን አጠናክራ መቀጠሏን ያነሱት ዶክተር ሳሙኤል የታላቁ ህዳሴ ግደብ ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለቀጣናው አገራት የኃይል ትስስር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።