የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከአገር ባለፈ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም እንዲሆን ለተጀመሩ ስራዎች ውጤታማነት የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለን -የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከአገር ባለፈ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም እንዲሆን ለተጀመሩ ስራዎች ውጤታማነት የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለን -የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ የምትኮራበት ዓለም አቀፍ ተቋም እንዲሆን የተጀመሩ ስራዎችን በማገዝ ረገድ የኦሮሚያ ክልል የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ለሚያስገነባው ዓለም አቀፍ የፖሊስ አመራር ኢንስቲትዩት ግንባታ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።
ግንባታውን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የሚያከናውነው ሲሆን 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ ፖሊስ ኢትዮጵያን አጽንቶ ካቆሙ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
አገራዊ ለውጡን ተከትሎም ጠንካራ የፖሊስ ተቋም ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲን ለማዘመን የተከናወኑ ስራዎችን በዚህ ረገድ ለአብነት አንስተዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችን በማብቃት ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በዜጎች ዘንድ የሚከበርና የሚወደድ ተቋም በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ግንባታው የተጀመረው ዓለም አቀፍ የፖሊስ አመራር ኢንስቲትዩትም ዩኒቨርሲቲው ከአገር ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተቋም እንዲሆን እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በይፋ የተጀመረው ግንባታም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ የምትኮራበት ዓለም አቀፍ ተቋም እንዲሆን የተጀመሩ ስራዎችን በማገዝ ረገድ የክልሉ መንግስት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ብቃት ያላቸውን የፖሊስ አመራሮች ከማፍራት ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃት ያለው የምርምር ተቋም ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ወደ ስራ ሲገባ ኢትዮጵያን የዘርፉ ምርምር ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ለአካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ የስራ እድል እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ምርጥ የፖሊስ አገልግሎት ከሚሰጡ አምስት የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ባለፈ በጅቡቲም ጭምር በስራ በመሰማራት ከ46 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ የኮንትራት ዋጋ ከ63 በላይ ፕሮጀክቶችን እየገነባ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ባላፉት አራት ዓመታትም የ67 ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ለደንበኞቹ ማስረከቡን ጠቅሰው፤ ዓለም አቀፍ የፖሊስ አመራር ኢንስቲትዩት ግንባታን በተያዘለት ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ግንባታ በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን አንድ ባለስድስት ወለል ህንጻ፣ የአመራር መኖሪያ ቤቶች፣ የተለያዩ የስብሰባ አዳራሾችን ጨምሮ ሌሎችንም ግንባታዎች በውስጡ የያዘ መሆኑ ተገልጿል።