ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራች ነው - የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራች ነው - የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራች መሆኑን የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ገለጸ፡፡
የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የመጠቀም፤ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎችን ብዜትና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡
በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀምን ለመከላከል አዋጅ ቁጥር 780/2005 እንዲሁም ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ብዜትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1132/2011 ሥራ ላይ ውለዋል፡፡
የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ እንዳለ አሰፋ፤ የተቋሙ ተልዕኮ ዘርፈ-ብዙና ጠንካራ ትብብሮችን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም፤ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍና ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ብዜትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል ተልዕኮውን ለመወጣት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የተሟላ ሕግ፣ በቂ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ አላከናወነችም በሚል ስሟ ይነሳ እንደነበር አስታውሰዋል።
እ.ኤ.አ በ2015 ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ-ኃይል ባወጣው ሪፖርት መሰረታዊ ጉድለቶች መኖራቸውን ያመላከተበት አጋጣሚ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የዓለም ሰላምና ስጋት የሆኑ ወንጀሎችን መከላከል የሚቻለው ጠንካራ የሀገር ውስጥ ተቋማትን በመገንባትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት መሆኑን በማመን አሁን ላይ በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ160 በላይ ሀገራት አባል የሆኑበት የፋይናንስ ተቋማት ሕብረት ኢግመንት ግሩፕ እና የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የፀረ-ፋይናንስ ወንጀሎች ግብረ-ኃይል ደረጃ የተሟላ ሕግ አውጥታ ወደ ሥራ ገብታለችም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጎችን በማውጣት፣ የተሟላ ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮችንም ዘርግታለች ነው ያሉት።
ለተፈጻሚነቱም ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋማት ሕብረትና የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የፀረ-ፋይናንስ ወንጀሎች ግብረ-ኃይል ላይ በአባልነት በመሳተፍ መረጃ እየተለዋወጠች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተቀናጀ የተቋማት ሥራና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በምታደርገው የመረጃ ልውውጥ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር ስለመቻሏም አቶ እንዳለ ጠቅሰዋል።
የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ሕገ-ወጥ ሀዋላ፣ ግብር ስወራ፣ ሙስና እና መሰል የፋይናንስ ወንጀሎች ላይ 177 የወንጀል ጉዳዮችን ለሕግ አስከባሪ አካላት ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል፡፡