በእርሻ ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች 19 ሺህ ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በእርሻ ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች 19 ሺህ ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አስታወቀ
ባህር ዳር፤ ግንቦት 15 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች 19 ሺህ ሄክታር መሬት አዘጋጅቶ ለአልሚ ባለሃብቶች እየሰጠ መሆኑን የክልሉ መሬት ቢሮ አስታወቀ።
ባለሃብቶች በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት መሰማራት በሚፈልጉበት አካባቢ ሁሉ መሬቱ ተዘጋጅቶ ህጋዊ አሰራርን መሰረት በማድረግ እየተመቻቸ እንደሚገኝ የቢሮው የገጠር መሬት ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ በላይ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከተዘጋጀው መሬት ውስጥም 12 ሺህ ሄክታሩ በመስኖ፣ በዘር ብዜት፣ በቅመማቅመም፣ በቡና፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በእንስሳት እርባታና በንብ ማነብ የስራ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች በምደባ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።
ቀሪው 7 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆንና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሰብል ልማት ላይ ለሚሰማሩ አልሚ ባለሃብቶች በውድድር ለመስጠት የጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም በቡና፣ በመስኖ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለሚሰማሩ አልሚዎች ከ6 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በምደባ መተላለፉን ጠቅሰዋል።
መሬቱ ለአልሚዎቹ የተላለፈው በስራ ዕድል ፈጠራ፤ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ሌሎች መመዘኛዎችን አሟልተው ለቀረቡ እንደሆነም ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ባለሃብቶቹ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በማልማት ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለአካባቢው አርሶ አደሮች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የቤአይካ ጠቅላላ ንግድ ስራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሰሜን ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ክንድይሁን እገዘው በሰጡት አስተያየት፤ በአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ 4ሺህ ሄክታር መሬት በመረከብ ወደ ልማት መግበታቸውን ተናግረዋል።
ከተረከቡት የእርሻ መሬት ውስጥ እስካሁን ከ3ኛ ወገን ነፃ የሆነ 350 ሄክታር መሬት በዘንድሮው የበጋ ወቅት ስንዴን በመስኖ አልምተው ምርቱን እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኙ ሰብሎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በእንስሳት እርባታና በዓሳ ሃብት ልማት ዘርፎች ለመሰማራት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዚገምና በምስራቅ ጎጃም ጎዛምን ወረዳዎች በጨረታ ቀደም ሲል አሸንፈው ከተረከቡት መሬት ውስጥ 300 ሄክታር ማልማታቸውን የተናገሩት አቶ በሪሁን አበራ ናቸው።
ካለሙትም ውስጥ በቆሎ፣ አኩሪ አተርና ማሾ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
የክልሉ መሬት ቢሮ ሰሞኑን ለጨረታ ካወጣው መሬት ተወዳድረው በማሸነፍ ተጨማሪ መሬት ወስደው ለማልማት እንደተዘጋጁም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ቀደም ሲል በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ 1 ሺህ 525 ባለሃብቶች 200 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ተረክበው እያለሙ እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።