መንግስት ዜጎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ዜጎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ):- መንግስት ዜጎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር 'ማህበራዊ ጥበቃ ለአገር ግንባታ በኢትዮጵያ' በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሀገራዊ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ነው።
በጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ጫናዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡
በኢትዮጵያም መሰል ችግሮች ፈተና እንደሆኑ ገልጸው፤ መንግስት ለዜጎች ማህበራዊ ችግሮች ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀትና በስፋት የስራ ዕድል መፍጠር ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዜጎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማደራጀት ድህነትን በሚቀነሱና ምርታማነትን በሚያሻሽሉ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለማህበራዊ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ማህበራዊ ጥበቃ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ቀውሶችን የሚቀርፍ፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር መሰረት የሚጥልና የመንግስትና ሕዝብን ማህበራዊ ውል የሚያጠናክር ቁልፍ ተግባር መሆኑን ነው አቶ ደመቀ ያብራሩት።
የሕጻናት ማቆያ ማዕከላት በማስፋፋት፣ ጎዳና የወጡ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም፣ ጧሪና ቀባሪ የሌላቸው አረጋዊያን በመደገፍ የተከናወኑ ስራዎች ይበል እንደሚያሰኙ ጠቅሰዋል።
ከዚህ አኳያ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ፖሊሲዎችን በውጤታማነት በመተግባር ተገማች ባልሆነው ዓለም የዜጎችን ጥቅም ለማስከበር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሰለባ የሆኑ ሕብረተሰብ ክፍሎች ዘላቂ ማህበራዊ ጥበቃ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድም የገጠርና የከተማ ሴፍትኔት መርሐ-ግብርን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ያም ሆኖ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ብዛት፣የፋይናንስ እጥረት፣ የቅንጅት አሰራርና ማህበራዊ ጥበቃ ግንዛቤና ቁርጠኝነት ማነስ የዜጎችን የማህበራዊ ጥበቃ ሽፋን፣ ፍላጎትና ጥራት ላይ ውስንነት መፍጠሩን ገልጸዋል።
የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የማህበራዊ ጥበቃ ሽፋን በማጠናከር የዜጎችን ኑሮ ማሻሻልና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሻሻሉ መሆናቸውን ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ሕልምን ዕውን ለማደረግ በሚደረገው ጥረት የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ተደራሽ በማድግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኡስማን ዲዮን በበኩላቸው፤ማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ለማጠናከር የሚተገበሩ ፕሮግራሞች የድሃ ዜጎችን ኑሮ ደረጃ በማሻሻልና የሰው ሀብት በማልማት ለአገር ግንባታ ሂደት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መሰረት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይ በኢትዮጵያ የሚተገበሩ ድህረ ጦርነት የመልሶ ግንባታ ስራዎች ለማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ነው ያሉት።
ማህበራዊ ጥበቃ የመንግስትና ሕዝብ ማህበራዊ ውል ማጎልበት፣ ለሰላምና መረጋጋት፣ ሰላማዊ ሕብረተሰብ በመገንባት እና ድህነትን በዘላቂነት መቅረፍ ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተው፤ ለማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት መጠናከር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር የሚተገብራቸው የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ተደራሽነት፣ የገንዘብ ድጋፍ፣ ጥራት፣ በማሳደግ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ ዓለም ባንክ ድጋፉን እንደሚቀጥል መው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
ሰላማዊ፣ አንድነቷ የተጠበቀና የበለፀገች ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ ) የኢትዮጵያ ተወካይ አቡበከር ካምፖ በበኩላቸው የሴቶችንና ታዳጊዎችን ጨምሮ አካታች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ፣ ከትውልድ ትውልድ እየተንከባለለ የመጣን ድህነትን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ማህበራጥ ጥበቃ አገልግሎት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ሕብረተሰብ ክፍሎችን በትምህርትና በሌሎች መሰረተ ልማት ተደራሽ በማድረግ ማህበራዊ ቀውስ የመቋቋም አቅም ለመገንባት እንደሚያያስችል ተናግረዋል።
ለአገር ግንባታ ካለው ሁለንተናዊ ፋይዳ አንጻር ማህበራዊ ጥበቃ ስርዓቱን ገቢራዊ ማድረግ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል።