ቀጥታ፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ከአፍሪካ የጉምሩክ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ):- የጉምሩክ ኮሚሽን ከአፍሪካ የጉምሩክ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።

የናይጀሪያ የገንዘብ፣ በጀትና ብሔራዊ እቅድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች በጉምሩክ ኮሚሽን የልምድ ለውውጥና ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል።

የጉምሩክ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሌ አብዲሳ ኮሚሽኑ ከአፍሪካ የጉምሩክ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራ መሆኑንና ይህም የንግድ ስርዓቱን ለማሳለጥና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለው አበርክቶ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የጉምሩክ አገልግሎት ዓለም አቀፋዊ ባህሪይ ያለው በመሆኑ ለሕገ -ወጥ ንግድና ድንበር ዘለል ወንጀሎች ተጋላጭ በመሆኑና እነዚህን ወንጀሎች ለመቀነስ የልምድ ልውውጡ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የኮሚሽኑን የአገልግሎት አሰጣጥ የሚያዘምኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሰራሮችን መተግበራቸውን አስረድተው የሪፎርም ስራዎቹ የንግድ እንቅስቃሴው ፈጣን እንዲሆን ከማድረጋቸው በተጨማሪ በገቢ አሰባሰብ እድገት ላይም ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል ነው ያሉት።

የናይጄሪያ ልዑካን ቡድን መሪ መሐመድ ዓሊ በበኩላቸው፣ ናይጀሪያ ከአፍሪካ አገራት መካከል ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗን አንስተዋል።

የልምድ ልውውጡ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከርና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን መግለጻቸውን ከጉምሩክ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም