የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 21ኛ መደበኛ ስብስባውን እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 21ኛ መደበኛ ስብስባውን እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ):-የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ21ኛ መደበኛ ስብሰባው የትምህርት ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ላይ እየተወያየ ነው።
በዘንድሮ ዓመት 240 ሺህ ለሚደርሱ የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በበይነ መረብ የመውጫ ፈተና ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።
በ2015 በመጀመሪያ ዲግሪ ኘሮግራም ለሚመረቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እቅድና የፈተና የክፍያ ተመን ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
የመውጫ ፈተናን ለመተግበር የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት ሚኒስትሩ የመውጫ ፈተና ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ መመሪያና የድርጊት መርሐ-ግብር ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
በመውጫ ፈተና የሚካተቱ የትምህርት ዓይነቶች (ኮርሶች) ተለይተው፤ በቅድመ-ምረቃ በሚሰጡ በሁሉም የትምህርት መስኮት የፈተና ንድፍ ማሳያ መዘጋጀቱንም ነው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ያብራሩት።
በሌላ በኩል የፈተና አሰጣጥ ስርዓት ስብራትን ለማረም በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በጥብቅ ዲስኘሊን በመምራት ከኩረጃ በፀዳ መንገድ መስጠት በመቻሉ ስርቆትንም ሆነ ኩረጃን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መከላከል ተችሏል ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የ2015ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በመጪው ሐምሌ ወር አጋማሽ ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብስባው የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።