በምእራብ ጉጂ ዞን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በምእራብ ጉጂ ዞን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ
ነገሌ ግንቦት 15/2015 (ኢዜአ) በምእራብ ጉጂ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተካሄደው የአንድ ወር ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን የዞኑ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የሚዲያና መረጃ ባለሙያ ቡድን መሪ አቶ ተመስገን ባቲ ከሚያዝያ 20 እስከ ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተካሂዷል ብለዋል፡፡
ቡሌ ሆራ እና ቀርጫ ሁለት ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ የዞኑ 11 ወረዳዎች የመርሃ ግብሩ የቦንድ ሽያጭ የተካሄደባቸው ከተሞች እንደነበሩም አመልክተዋል፡፡
የዞኑ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ባለሀብቶች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በድጋፉ መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ እስካሁን ከተካሄደው የቦንድ ሽያጭም 6 ሚሊዮን 729 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡
ለተከታታይ አመታት የተካሄደው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስኬታማ የውሃ ሙሌት የዞኑን ህዝብ ለድጋፍና ትብብር ያነሳሳ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ቡድን መሪው አክለውም የዞኑ ህዝብ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ወደፊትም አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት 9 ወራት ብቻ ለግድቡ ግንባታ ከዞኑ ህዝብ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ከነበሩና በዞኑ የፍንጭ ውሃ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ባቲ ደጊጫ በሰጠው አስተያየት የግድቡን ግንባታ ተባብረን እንደጀመርን እንጨርሰዋለን ብሏል፡፡
ባለፉት ዓመታት በግል ፍላጎትና ተነሳሽነት በ3 ዙር ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የ2 ሺህ ብር ቦንድ መግዛቱን ወጣቱ አስታውሷል፡፡
አሁንም "እኔም የድርሻዬን" በሚል መሪ ሐሳብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ሲካሄድ የ2 ሺህ ብር ቦንድ መግዛቱን ገልጾ፤ ድጋፉን ወደፊትም እቀጥልበታለሁ ብሏል፡፡
የዚሁ ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪና የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ወጣት ያተኒ ሚጦ የህዳሴ ግድብን መጠናቀቅ በጉጉት እየተጠባበቀ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ወጣቱ በእርሻ ስራ ከሚያገኘው ዓመታዊ ገቢ በመቀነስ በ"እኔም የድርሻዬን" መርሃ ግብር የአንድ ሺህ 500 ብር ቦንድ መግዛቱን አመልክቷል፡፡
የህዳሴ ግድብ የማንነታችን መገለጫ መሆኑን በመገንዘብ በየዓመቱ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሳደርግ ቆይቻለሁ፤ እስከመጨረሻም አላቆምም ብሏል፡፡
የግድቡ ተከታታይ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ እንደጀመርን ተባብረን ለመጨረስ የሚያስችል አቅም የፈጠረ ነው ነው ሲሉም ተናግረዋል አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡