ቀጥታ፡

ለሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት የአመራሩ አንድነትና ቅንጅታዊ አሰራርን ይጠይቃል -ዶክተር ፍጹም አሰፋ

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ):-  ለሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት የአመራሩ አንድነትና ቅንጅታዊ አሰራርን ይጠይቃል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ተናገሩ።

በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሁለተኛው ምዕራፍ ዕቅድ ላይ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተቋማት ኃላፊዎች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች አባላት በተገኙበት ውይይት እየተካሄደ ነው። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ አዳዲስ ተግዳሮቶችን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚን ለመገንባት ተጨማሪ አገራዊ የኢኮኖሚ ልማትና ብልፅግና ማስፈጸሚያ ዕቅድ በማስፈለጉ ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም. የሚተገበር ሁለተኛ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ለውጡ ካሉት አራት ምሰሶዎች አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚን ማጠናከርና ማረጋጋት ሲሆን፤ ለዚህም ስኬት የተሻለ የሀብት አሰባሰብና ውጤታማ የመንግስት ወጪና ኢንቨስትመንት አስተዳደር ለመፍጠር እቅድ ይዟል።

በተጨማሪም ዘላቂ የዕዳ አስተዳደርን መፈጸም፣ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን ማስፈንና የፋይናንስ ዘርፍ ለውጥና  ተደራሽነትን ማሳካት በእቅድ ውስጥ ተካቷል። 

ሁለተኛው የለውጡ ምሰሶ የኢንቨስትመንትና የንግድ ከባቢን ማሻሻል መሆኑን የገለጹት ዶክተር ፍጹም ይህን ለማሳካት የተሻሻለ ገበያ ተደራሽነትና ተወዳዳሪነት፣ ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ የተነቃቃ የጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ፣ ጥራት ያለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ግብ መያዙን አመልክተዋል። 

የክህሎት ልማትና የተሻሻለ የሰው ኃይል ገበያ እንዲኖር መታቃዱን ተናግረዋል።

ሶስተኛው ምሰሶ የዘርፎችን አቅም፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የተሻለ የግብርና ምርታማነት እና ኢንቨስትመንት፣ የተሻለ የቤቶችና ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማትና ኢንቨስትመንት ላይ በትኩረት ይሰራል።

እንዲሁም የተሻለ የማዕድን ምርታማነትና ኢንቨስትመንት፣ የውጭ ንግድን ማሳደግ፣ የኢትዮጵያን የበጎ ገፅታ ግንባታ የቱሪስት መዳረሻ ልማትና የዲጂታል ኢኮኖሚ አቅምን ማበልጸግ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል። 

አራተኛው ምሰሶ የመንግሥትን የመፈጸም አቅም መጎልበት ለዚህም ብቁና ውጤታማ የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት መፍጠር፣ ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ውጤታማና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት፣ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ ዲጂታል መረጃ አሠራርን የመተግበር ግቦች መኖራቸውን ነው ሚኒስትሯ ያነሱት። 

ለለውጡ ትግበራና ስኬት አመራሩ የልማት ፋይናንስን በማሳደግ፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ገበያን ማዘመን፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል። 

ለሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ለውጥ ስኬት የአመራሩ አንድነት፣ የጋራ  ራዕይ ሊኖረው ይገባል ብለዋል። 

አመራሩን ጨምሮ ሁሉም በየደረጃው ለሰላም ዘላቂነት የበኩሉን በመወጣት ለኢኮኖሚ ለውጡ መሳካት እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።  

በለውጡ የመጀመሪያ 12 ወራት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለመፍጠር እንደሚሰራና  ከ12 እስከ 36 ወራት ተወዳዳሪነትን ማጎልበት፣ የግሉን ዘርፍ ማጠናከርን ያሳካል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል። 

በረዥም ጊዜ ደግሞ በ10 ዓመቱ ዕቅድ የተያዙ ግቦችን በማሳካት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት የራሱ ሚና እንደሚኖረው ነው ዶክተር ፍጹም ያመለከቱት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም