ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የበለጸገችና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን ለመፍጠር የምታበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የበለጸገችና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን ለመፍጠር የምታበረክተውን አስተዋጽኦ  አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ። 

የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የበለጸገች፣ በምጣኔ ኃብት ያደገች፣ ለሕዝቦቿ ምቹ አፍሪካን ለመፍጠር አንድነትና ኅብረትን ማጠናከር ይገባል።

በአፍሪካ አንድነትን ለማጠናከርና የምጣኔ ኃብት እድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

በተለይም ምጣኔ ኃብታዊ ውህደትና ትስስር ለማረጋገጥ በጅምር ላይ ያለው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናን ትግበራ ማፋጠን እንደሚገባም ጠቁመዋል። 

አፍሪካ ያላት የተፈጥሮ ኃብትና አምራች የሰው ኃይል ለዕድገቷ እድል መሆናቸውን አንሰተው እነዚህን ኃብቶች በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

የአህጉሪቷን  እድገት  ወደኋላ የሚጎትቱ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀትም አፍሪካዊ መፍትሄ ለአፍሪካዊ ችግር መርህን ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፓን አፍሪካን ጽንሰ ኃሳብ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አምባሳደር ምስጋኑ አንስተዋል።

ኢትዮጵያም የበለጸገችና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን ለመፍጠር የምታበረክተውን አስተዋጽኦ  አጠናክራ እንደምትቀጥል ሚኒስትር ዴኤታው አረጋግጠዋል።

በፓናል ውይይቱ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች፣ የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች፣ ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም