የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

175

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

በመርሐ-ግብሩ መሰረት ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሃዋሳ ከተማ በ33 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን በ44 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ሃዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ሁለት ጊዜ ተሸንፏል በሶስቱ አቻ ወጥቷል።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ መድን ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

ሌላኛው የ25ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር የመጨረሻው ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክና መቻል መካከል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በ11 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። መቻል በአንጻሩ በ32 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። በአራቱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዛሬው ጨዋታ ከተሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን የሚያረጋግጥ ሁለተኛ ክለብ ይሆናል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከቀናት በፊት ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱ የሚታወስ ነው።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወቃል።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን 1 ለ 0  እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም