ቀጥታ፡

የተለያዩ ችግሮችን በመከላከል የኢኮኖሚ ዕድገቱን ጤናማ ለማድረግ የአመራሩ ቅንጅታዊ አሠራርና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015 (ኢዜአ) የኑሮ ውድነትን፣ ሕገ-ወጥ ንግድንና የፀጥታ ችግርን በመከላከል የኢኮኖሚ ዕድገቱን ጤናማ ለማድረግ የአመራሩ ቅንጅታዊ አሠራርና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል ተባለ።

የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የመንግሥት የየዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸም ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የምክር ቤት አባላትና የተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል። 
 

የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ፤ በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 5 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ አመላካቾች መኖራቸውን ተናግረዋል። 

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ በርካታ ጫናዎችን ተቋቁሞ ስኬት ቢያስመዘግብም አሁንም ያልተሻገርናቸው ፈተናዎች አሉ ብለዋል። 

በተለይም ሀገርና ሕዝብን የሚጎዱ ሕገ-ወጥ ንግድና ኬላ፣ የኑሮ ውድነትና የፀጥታ ችግሮች ቢኖሩም እነዚህን ችግሮች በመቆጣጠር በኩል የፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ችግር መኖሩን ገልጸዋል።
 

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ፤ ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆና ውጤታማ ሥራ መሠራቱን አንስተዋል። 

በበርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሁም በዓለም አቀፍና በውስጥ ችግሮች እየተፈተነችም ቢሆን የማይበገር ኢኮኖሚ እየገነባች ነው ብለዋል። 

በቀጣይ የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛን ለማስጠበቅ የዋጋ ግሽበትን እና የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ በየዘርፉ ያለው አምራችና አገልግሎት ሰጪ በኃላፊነት እና በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ፤ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ የውጭና የሀገር ውስጥ ንግድ ሥርዓቱን እየፈተኑ መሆኑን ገልጸዋል።  

መንግሥት በዚህ ረገድ ሰፋፊ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አንስተው፤ የሀገር ውስጥ ንግድ መዛባትን የሚያስከትሉ የሥራ መደቦች እንዲሰረዙ ተደርገዋል ብለዋል። 

የንግድ ሰንሰለቱ መራዘሙን ተከትሎ መሠረታዊ ሸቀጥ አትክልትና ፍራፍሬ ዝውውር ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍም ከክልሎች ጋር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
 

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፤ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየጎዳ በመሆኑ ለመከላከል ከጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል። 

በርካታ ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ  እየተወጡ አለመሆኑ፣ አመራሩና ሕጋዊ ነጋዴዎች በኮንትሮባንድ እየተሳተፉ መሆናቸውና  ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው አንስተዋል። 

በዚህም ባለፉት ወራት 53 ቢሊየን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን በመጥቀስ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት አብራርተዋል። 

አደጋውን ለመቆጣጠር የሎጂስቲክስና የቴክኖሎጂ አቅሞች ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡ የወጪና ገቢ ንግድ ምርቶችን በከፍተኛ ብቃት መፈተሽ የሚያስችል ሥርዓት እንደሚጀመር ጠቁመዋል። 

በቀጣይ ችግሩን ለመቀልበስ የፀጥታና የፍትሕ ተቋማት ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠርና እርምጃ በመውሰድ ሂደት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል። 

የኮንትሮባንድ ንግድ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል የኃይል እርምጃን መውሰድ የሚችል የተቀናጀ የፀጥታ ተቋማት መዋቅር መፈጠሩንም አንስተዋል።
 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ፤ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት  ባስመዘገብነው ውጤት ሳንረካ በቁርጠኝነት መሥራት ይኖርብናል ብለዋል። 

ለዚህም ቅንጅታዊና የጋራ ሥራን መተግበር፣ ችግሮችን  ወደ ውጭ ከመግፋት ይልቅ ተጋፍጠን በጋራ መፍታት ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም