ኢትዮጵያ የዓረብ ሊግ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ያስተላለፈውን የውሳኔ ሐሳብ እንደማትቀበለው ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዓረብ ሊግ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ያስተላለፈውን የውሳኔ ሐሳብ እንደማትቀበለው ገለጸች
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በዓረብ ሊግ የመሪዎች ጉባኤ የተላለፈው የውሳኔ ሐሳብ እንዳሳዘናት እና በፍፁም እንደማትቀበለው አስታወቀች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባወጣው መግለጫ፣ “በቅርቡ በተካሄደው የዓረብ ሊግ የመሪዎች ጉባኤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የተላለፈው የውሳኔ ሐሳብ ግብፅ የምታራምደውን አቋም የሚያስተጋባ በመሆኑ ኢትዮጵያን አሳዝኗታል” ብሏል።
ይህ የውሳኔ ሐሳብ የግድቡን ጉዳይ በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት እና አስታራቂ ሐሳብ ለማምጣት እየሠሩ ያሉትን የአፍሪካ ኅብረት እና አባል ሀገራቱን ጥረት ያንኳሰሰ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው የጠቆመው።
ከዚህም በተጨማሪ የውሳኔ ሐሳቡ ከአፍሪካ እና ከዓረብ ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ታሪክ ጋር በተፃራሪ የቆመ ነው ብሏል።