ሀገር በቀል እውቀቶችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመደገፍ ለዘላቂ ሰላም ለማዋል እየተሰራ ነው- ትምህርት ሚንስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል እውቀቶችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመደገፍ ለዘላቂ ሰላም ለማዋል እየተሰራ ነው- ትምህርት ሚንስቴር
ደሴ ግንቦት 14/2015(ኢዜአ) ፡- ሀገር በቀል እውቀቶችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመደገፍ ዘላቂ ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ወሎ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስ፣ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ጥናት ኮንፈረንስ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል፡፡
በሚኒስቴሩ የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰለሞን ቢኖር በኮንፈረንሱ ላይ ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የነበረውን ስርዓተ ትምህርትና የምርምር ስነ-ምህዳር ክፍተት ለመሙላት በሚያስችል መልኩ የሀገር በቀል እውቀቶችን ማካተት የሚያስችል የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የቀደምት ስልጣኔ መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ የሽምግልና እርቅ ስርዓት፣ ባህላዊ የመድሃኒት ቅመማ፣ የኪነ ጥበብና ሌሎችም ሥራዎች የሀገር በቀል እውቀት ውጤት መሆናቸው ህያው ምስክር ናቸው ብለዋል፡፡
በሪፎርሙ ላይም ሀገር በቀል እውቀቶችን በመለየትና በማሳደግ ለሀገር ግንባታ ለማዋል በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ ለማከናወን የአቅም ግንባታ ላይ ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል።
የሀገር በቀል እውቀቶችን በህግ ማዕቀፍ በማስደገፍ መሰነድ፣ ማበልጸግ፣ ማስተማርና ማሳወቅ፣ መጠቀምና ለትውልድ ማስተላለፍ ዩኒቨርሲቲዎች በማህበረሰብ አገልግሎት ስራቸው ትኩረት ሰጥተው መስራት ያለባቸው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ትኩረት ለተሰጠው የኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት፣ ሰላምና እድገት የሚኖረውን ፋይዳ ለማሳደግ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ሌላውም አካል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር መላኩ ታመነ ፤ የሀገር በቀል እውቀቶች ለዘላቂ ልማትና ሰላም ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
በዚህም የወሎን አብሮነት፣ የመቻቻልና የፍቅር ተምሳሌት፣ የአባቶችን የሽምግልና ስርዓት፣ ባህላዊ መድሃኒት ቅመማ፣ የዕደ ጥበብና ስነ ህንጻ ሥራዎች በቴክኖሎጅ በመደገፍና በማበልጸግ ለትውልድ እንዲተላለፉ እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እስካሁንም የወሎ ጋቢ፣ የወሎ የብረት ሳፋ፣ የወሎ ጭስና ሽቶን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ አስደግፎ በማምረትና "ብራንድ " በማሰጠት የተሻለ ጥቅም እንዲሰጡ መደረጉን ማሳያነት አንስተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለሀገር በቀል እውቀት የሰጠው ትኩረት የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ደግሞ ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ምህድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ኤርሚያስ ገብረ ኪዳን ናቸው፡፡
ለአደጉ ሀገራት የስልጣኔ ምንጭ የሆናቸው ሀገር በቀል እውቀት መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያም ያላትን ሀገር በቀል እውቀት በትምህርት ስርዓቱ በማካተት በቴክኖሎጂ ጭምር ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ሀገር በቀል እውቀት እንደየ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ በመቃኘት መተግበርና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ፤ ምሁራንም በምርምር በማገዝ ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርስ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡