ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አባላት የእውቀት፣ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ተመለከተ

398

ጅማ ግንቦት 14/2015 ( ኢዜአ)  ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ አባላት የእውቀት፣ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስገነዘበ።

በሀገር ውስጥ በርካታ ተቋማት የቴክኖሎጂና የአቅም ግንባታ ስልጠና ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም በውጭ የሚኖረው ዳያስፖራ ማሕበረሰብ የሚያደርገው ድጋፍ የተቀናጀ አለመሆኑ ተመልክቷል።

በዚሁ ጉዳይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከጅማ፣ ከሀዋሳ፣ ከጂግጂጋ እና ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አንድ አመት የፈጀ የዳሰሳ ጥናት ይፋ አድርጓል።

የጥናቱ አላማ የተማረው ዳያስፖራ እውቀቱን፣ ክህሎቱንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተቀናጀና በተደራጀ ሁኔታ ሀገሩን ማገዝ እንዲችል ያለውን መልካም አጋጣሚ መለየት ነው ተብሏል።

የጥናቱ አስተባባሪና በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር መኮንን ቦጋለ እንዳሉት በጥናቱ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና የዲያስፖራ ቢሮ ተዳሷል።

የጥናትና ምርምር ትብብር፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ የቴክኖሎጂ ማእከላት ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ የጤና መመርመሪያ ማእከላት ግንባታ እና በዲፕሎማሲው ዘርፍም የዳያስፖራው እገዛ እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ተመላክቷል ብለዋል።

በጥናቱ 103 የፕሮፌሽናል ዲያስፖራ ማህበራት ተወካዮች የተጠየቁ ሲሆን ሀገራቸውን የማገዝ ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም በምን እና እንዴት ማገዝ እንዳለባቸው ለይተው አላስቀመጡም ነው ያሉት።

ሌላው የጥናቱ አስተባባሪ አቶ ጥበቡ ታፈሰ በበኩላቸው ከሀገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊውያን በተቀናጀና በተናበበ መንገድ ሀገራቸውን ማገዝ እንዲችሉ ጥናቱ መሰራቱን ተናግረዋል።

በተለይም በተለያዩ የውጭ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ያላቸውን ክህሎት ፣እውቀትና የቴክኖሎጂ  በማሸጋገር በእናት ሀገራቸው እድገትና ብልፅግና ጉዞ በመሳተፍ አስተዋጽዎ እንድያደርጉ ለማስቻል ያለመ ጥናት ነው ብለዋል።

አብዛኛው የዳያስፖራው ማህበረሰብ ሀገሩን በማንኛውም ሁኔታ ለማገዝ ቀናኢ መሆኑን ያነሱት አቶ ጥበቡ ይህንን ሀብት ማቀናጀትና በታቀደ አሰራር ለመተግበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በውጭ የሚኖሩ ዜጎች መብት የህግ ከለላ ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ገዛኸኝም እንዲሁ የዳያስፖራውን ማሕበረሰብ በማቀናጀት ለሀገሩ ተገቢውን እገዛ እንዲያደርግ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሀገሩን የሚወድ ዳያስፓራ በአጠቃላይ ለሀገሩ የሚያደርገው ነገር ትልቅ ትርጉም እንዳለው በመገንዘብ ለሀገራቸው እውቀትንና ቴክኖሎጂን ለማሸጋገር መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በዘመኑ በየትኛውም ዘርፍ የቴክኖሎጂ አበርክትዎ እየጎላ በመምጣቱ በተበታተነ መንገድ ሲደረግ የነበረውን ጥረት አቀናጅቶ ለመፈጸም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ይፋ ማድረጊያ መድረክ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በቀረበው ጥናት ግኝት መሰረት ተወያይተው ስለአፈጻጸሙ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም