የፎረንሲክ ምርመራ ሥልጠና በአገር ውስጥ ለመጀመር የኢንስቲትዩት ግንባታ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፎረንሲክ ምርመራ ሥልጠና በአገር ውስጥ ለመጀመር የኢንስቲትዩት ግንባታ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015 (ኢዜአ)፡-በውጭ አገራት ሲሰጥ የነበረውን የፎረንሲክ ምርመራ ሥልጠና በአገር ውስጥ ለመስጠት የፎረንሲክ ኢንስቲትዩት በማስገንባት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የፕሮጀክት አስተዳደር ዋና ክፍል ተወካይ ኮማንደር ስንታየሁ ለገሰ፤ በተለያዩ የውጭ አገራት ሲሰጥ የነበረውን የፎረንሲክ ሥልጠና በአገር ውስጥ ለመጀመር የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በ1 ቢሊየን 282 ሚሊየን ብር የፎረንሲክ የኢንስቲትዩት ግንባታ መጀመሩን ተናግረዋል።
የኢንስቲትዩቱ ግንባታ በአገሪቷ ዘመናዊ ፖሊስ ለመገንባት የተጀመረው ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁለት ዓመት ተኩል ግዜ ውስጥ ተጠናቆ ሥልጠናው የሚጀመር መሆኑን ገልጸዋል።
የዜጎችን ህይወት፣ ንብረትና የአካል ደኅንነት የመጠበቅ፣ ወንጀልን የመከላከልና በዘመናዊ ምርመራ ታግዞ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ማድረግ የፖሊስ ዓይነተኛ ሚና መሆኑን አብራርተዋል።
የፎረንሲክ ሳይንስ ዘርፈ-ብዙ ሳይንሳዊ ምርመራዎችን በማድረግ እውነታዎችን በማረጋገጥና አጥፊዎችን ለይቶ የሕግ ተጠያቂ ለማድረግ መሰረታዊ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም ፖሊስ በሁሉም መስክ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት ከዘመኑ ጋር የሚራመዱ ዘመናዊና ሳይንሳዊ አሠራሮችን ተግባራዊ እያደረገ ነው ብለዋል።
የኢንስቲትዩቱ ግንባታ እውን ሆኖ ሥራ ሲጀምርም የዲ.ኤን.ኤ ምርመራን ጨምሮ የአሻራ፣ የሰነድ ምርመራና ሌሎችንም የፎረንሲክ ምርመራ ሥልጠናዎች የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክት አስተባባሪ ረዳት ኮሚሽነር ለአ መኮንን፤ የፎረንሲክ ሥልጠናዎች በአብዛኛው በውጭ አገራት ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአገር ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሥልጠና ለመስጠትና ዘመናዊ የወንጀል ምርመራ ሥራን የሚያቀላጥፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱን ግንባታ እያከናወነ ያለው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ፕሮጀክት ማኔጀር አስቻለው ኬነሞ፤ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ በጥራት ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል።
የግንባታውን ሂደት ከተጀመረ ዘጠኝ ወራት ማስቆጠሩን ጠቅሰው፤ አፈጻጸሙ 22 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይም ሌሎች የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኑ ታውቋል።