የፈጠራ ባለሙያዎች በሚያጋጥሙ ፈተናዎች ሳይበገሩ ለአገር ዕድገት በውጤት ተኮር ሥራዎች ሊተጉ ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

372

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015 (ኢዜአ)፡-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የፈጠራ ባለሙያዎች በሚያጋጥሙ ፈተናዎች ሳይበገሩ በውጤት ተኮር ሥራዎች ሊተጉ እንደሚገባ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ 3ኛውን ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር መድረክ በዛሬው እለት በይፋ ከፍተዋል። 


 

የውድድር መድረኩ "ክህሎት ለተወዳዳሪነት" በሚል መሪ ሃሳብ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣይ አምስት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል። 

በውድድሩ የፈጠራ ሥራዎች አውደ-ርዕይ፣ የፓናል ውይይትና ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የውድድር መድረኩ  ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ብቃታቸውን ለማሳየትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ሁነኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በዕለቱ በተመለከቷቸው የፈጠራ ሥራዎችም ትልቅ ተስፋ መኖሩን ጠቅሰው፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወኑም አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ በሁሉም ኢኮኖሚ ዘርፎች የግብዓት እጥረት ስለሌለ የፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ሰዎች ማብዛትና ግብዓቶችን አመጋግቦ በመጠቀም ሀገር መለወጥ እንደሚቻል ተናግረዋል።

በመሆኑም ፈጠራ ነባር ነገሮችን በአዲስ የሚተካና የመፍጠር ክህሎት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ የችግሮች የመፍትሔ ቁልፍ የሆነውን ፈጠራ ፈጥኖ መቀበል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችን በድል ለመሻገር የፈጠራ ባለሙያዎች በሚያጋጥሙ ፈተናዎች ሳይበገሩ በውጤት ተኮር ሥራዎች ለአገር እድገትና ብልጽግና እውን መሆን ሊተጉ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የፈጠራ ባለሙያዎች የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እንደመስፈንጠሪያ በመጠቀም ውጤት ተኮር ሥራዎች ላይ አበክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፤ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች ከዕድገት ምንጭነታቸው ባሻገር ለተወዳዳሪ ኢኮኖሚና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

የክህሎት ውድድሩ የተዘጋጀውም በየደረጃው ባሉ የቴክኒክ ኮሌጆች ሦስት እርከን ውድድሮች አድርገው የተለዩ "የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር" ነው ብለዋል።

የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ለማዘመን ሚኒስቴሩ መጠነ-ሰፊ የለውጥ ሥራዎችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ሥር የሚገኘው የብየዳ ማዕከል ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ የዓለም አቀፉ የክህሎት ማኅበር አባል ለመሆን ሚኒስቴሩ ጥያቄ ማቅረቡንም ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በይፋ በተከፈተው የክህሎት ውድድር የክልሎች የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚመለከታቸው አካላትና የፈጠራ ባለሙያዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም