የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ያሏቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ ነው - አምባሳደር ዳዋኖ ከድር - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ያሏቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ ነው - አምባሳደር ዳዋኖ ከድር
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015(ኢዜአ):- የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ አምባሳደር ዳዋኖ ከድር ተናገሩ።
አምባሳደር ዳዋኖ ለኢዜአ እንደገለጹት የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።
በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም የቻይና ባለኃብቶችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በግብርና፣ በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ቻይና በፖለቲካ እንዲሁም በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንዲሁም የልማት ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ነው ያስረዱት።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተደረጉ የሕግ ማሻሻያዎች፣ ማበረታቻዎችና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተከናወኑ ሥራዎችን የማስተዋወቅ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህም ቻይናውያን በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት።
"በኢትዮጵያ በሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ 107 የቻይና ኩባንያዎች መሳተፋቸውን አስታውሰዋል።
በማምረቻ፣ በሲሚንቶ፣ በብረታብረት፣ በማዕድንና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብ ችለዋል ብለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1970ዎቹ የተጀመረው የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።