ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በዲጂታል ክፍያ ስርዓት ተላልፏል

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015(ኢዜአ):- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በዲጂታል ክፍያ ስርዓት መተላለፉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለፁ።

ሚኒስትሯ የመንግሥትን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸምን ለሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ለምክር ቤት አባላትና ለተቋማት ኃላፊዎች ባቀረቡበት ወቅት መንግሥት አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባት በዲጂታል ፋይናንስ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም በፖሊሲና በአሰራር በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በሞባይል ገንዘብ የማስተላለፍ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ60 ሚሊዮን በላይ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ1 ትሪሊዮን 220 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በዲጂታል ክፍያ መተላለፉን ጠቁመዋል።

ይህም ከ2014 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የ454 ነጥብ 31 ቢሊዮን የዲጂታል ገንዘብ ዝውውር ጋር ሲነፃፀር የ169 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ኢትዮጵያን ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።


 

ለአብነትም የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሙሉ ሙሉ ወደ ቴክኖሎጂ ስርዓት መግባቱን ጠቅሰዋል።

የታክስ ስርዓቱንም ወደ ኤሌክትሮኒክስ ክፍያ የማስገባት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ኢኮኖሚው ማህበረሰቡን ይበልጥ  ተጠቃሚ እንዲያደርግ ሰፊ የቴሌኮም መሠረተ ልማት በመዘርጋት የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢንተርኔት ተጠቃሚ ዜጎችን ቁጥር ለመጨመርም እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢንተርፕራይዞችን እና የተቋማት የእርስበርስና ከተገልጋዮች አኳያ የብሮድባንድ ተደራሽነትን ለማስፋት በተሠራው ሥራ የ19 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ የዲጂታል ኢኮኖሚና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ወጥነት ያለው፣ የተቀናጀና ተገቢው ቁጥጥር የሚደረግበት የዲጂታል ትግበራ ሊኖር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም