ካናዳ የኢትዮጵያን ልማት ስራዎችና ሰላምን የማጽናት ጥረቶች ልትደግፍ ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ካናዳ የኢትዮጵያን ልማት ስራዎችና ሰላምን የማጽናት ጥረቶች ልትደግፍ ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015(ኢዜአ):- ካናዳ የኢትዮጵያን የልማት ስራዎችና ሰላምን ለማጽናት የሚደረጉ ጥረቶች እንድትደግፍ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።
አቶ ደመቀ ከካናዳ ዓለም አቀፍ የልማት ሚኒስትር ሃርጂት ሲንግ ሳጃን ጋር ዛሬ ማለዳ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ ሁለቱ አገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ ጠንካራ ትብብራቸውን ይበልጥ በልማቱ መስክም ማጎልበት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ መንግስት ልማት በአገር ቤትና በቀጣናው ለማምጣት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚህም የኢንቨስትመንትና የንግድ ፖሊሲዎች በመደገፍ ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስሰር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ስትራቴጂካዊ አጋርነቶች እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።
የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳና የ2025 የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ በለውጥ ውስጥ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ምሰሶዎች ናቸው ብለዋል አቶ ደመቀ።
የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራና ሴቶችን ማብቃት በኢኮኖሚው መስክ ትኩረት ከተሰጣቸው ዋንኛ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበትም ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድም ካናዳ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የልማትና ሰላምን የማጽናት ጥረቶች ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ደመቀ ሰላም የየትኛውም የልማት ስራ የጀርባ አጥንት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሽግግር ፍትሕ ለማስፈን፣አገራዊ ምክክርና የተሃድሶ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ዓለም አቀፍ ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ለባለሀብቶች በግብርና ማቀነባበሪያ፣ማዕድን፣አምራች፣ቱሪዝምና ሌሎች መስኮች የተቀናጀ የኢኮኖሚ ምቹ ሁኔታ ወደ መፍጠር ምዕራፍ ሽግግር እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛው ምዕራፍ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ለመተግበር በትኩረት እየሰራች ነው ያሉት አቶ ደመቀ ግብርና፣ማዕድን፣አምራች ዘርፍ፣ታዳሽ ኃይልና ቱሪዝም ቁልፍ የልማት አንቀሳቃሾች በሚል ዋንኛ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።
መንግስት ቁልፍ ብሎ በለያቸው ዘርፎች ለዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችና የልማት አጋሮች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በቅርቡ ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የካርበን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት ስትራቴጂና ለተከታታይ ዓመታት እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አገር ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የካናዳ ዓለም አቀፍ የልማት ሚኒስትር ሀርጂት ሲንግ ሳጃን በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ያላቸውን የረጅም ጊዜ የልማት ትብብር አውስተው በዘርፉ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር አገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ካናዳ በኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እየታዩ ያሉ ለውጦችና ማሻሻያዎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የካናዳ የንግድ ዘርፍ ሊሳተፍባቸው የሚችሉ የኢኮኖሚ እድሎችን የያዘ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ካናዳ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎችና ሁሉን አቀፍ የልማት ጥረቶችን እንደምትደግፍ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አረጋግጠውላቸዋል።