ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ወደ ዴንማርክ የጀመረው በረራ የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ያሳድገዋል - የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኮፐንሀገን ዴንማርክ የጀመረው አዲስ በረራ የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት  ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ኮፐንሀገን ዴንማርክ አዲስ በረራ በትላንትናው እለት ማስጀመሩ ይታወሳል። 


 

በመርሃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ የማኔጅመንት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት፤ አየር መንገዱ በየጊዜው ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን በማስፋት የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚነትን በማሳለጥ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በያዝነው ወር በተከታታይ አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እያስተዋወቀ  ሲሆን፤ ወደ ኮፐንሀገን የተጀመረው በረራም በኢትዮጵያና በዴንማርክ መካከል የላቀ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያስገኛል ብለዋል።

እንዲሁም ዴንማርክና አፍሪካን በዲፕሎማሲና በኢኮኖሚው ዘርፍ  ለማስተሳሰርም የዚህ በረራ መጀመር ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የሰሜን አውሮፓና የደቡብ ስካንዲኔቪያን አገሮችንም  በማስተሳሰር ረገድ ይህ በረራ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ይህ በረራ ከአዲስ አበባ ወደ ዴንማርክ በሳምንት አምስት ቀናት የሚደረግ  ሲሆን፤ በሀገራቱ መካከል ዲፕሎማሲን፣ ኢንቨስትመንትና ንግድን እንዲሁም ቱሪዝምን ይበልጥ ለማሳደግ እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

አየር መንገዱ በተያያዘው ፈጣን እድገትም በዚህ ወር ብቻ በርካታ አዳዲስ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ያስጀመረ ሲሆን፤ በቅርቡም አቢጃንን ከኒውዮርክ ከተማ ለማገናኘት የሚያስችል አዲስ በረራ እንደሚጀምር ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ ካውንስለር ሲቭ ቢያት በበኩላቸው፤ ከአዲስ አበባ ዴንማርክ የተጀመረው በረራ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ  መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ በረራ እውን እንዲሆን ላስቻሉት ሁሉ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም