የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

356

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25 ሳምንት መርሐ-ግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

ፋሲል ከነማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ፋሲል ከነማ 37 ነጥብ 5 ሲሆን ሲዳማ ቡና 30 ነጥብ 12 ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ፋሲል ከነማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በአንጻሩ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ተሸንፏል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ፋሲል ከነማ 4 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው 25 ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ  መርሐ-ግብር ወልቂጤ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ  ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወልቂጤ ከተማ 29 ነጥብ 13 ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ 30 ነጥብ 11 ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፏል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ 25 ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሀዲያ ሆሳዕና ባህር ዳር ከተማን እንዲሁም የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን በተመሳሳይ 2 1 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም