76ኛዉ የአለም ጤና ጉባኤ በስዊዘርላንድ ጀኔቫ መካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
76ኛዉ የአለም ጤና ጉባኤ በስዊዘርላንድ ጀኔቫ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015(ኢዜአ)፦ ዓመታዊውና 76ኛዉ የዓለም ጤና ጉባኤ በስዊዘርላንድ ጀኔቫ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
የዘንድሮዉ የዓለም ጤና ጉባኤ “የዓለም ጤና ድርጅት 75 ዓመት ቆይታ፣ ህይወትን በማዳን፣ ጤና ለሁሉም ለማሳካት” (WHO at 75: Saving lives, driving health for all) በሚል መሪ ሀሳብ ነው መካሄድ የጀመረው።
ኢትዮጵያም በጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በተመራ እና ከፌዴራልና ከክልል ጤና ቢሮዎች በተዉጣጣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ባካተተ ልዑክ ተወክላ በጉባኤው ላይ እየተሳተፈች ተገኛለች።
በልዑካን ቡድን ውስጥ የግሉ ጤና ዘርፍ ተወካዮች መካተታቸውም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጄኔቭ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን በጉባኤዉ ላይ እየተሳተፈ መሆኑም ተገልጿል።
76ኛ የዓለም ጤና ጉባኤ ለሚቀጥሉት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን የተለያዩ ጤና እና ጤና ነክ ጉዳዮች ተነስተው ምክክር ይደረግባቸዋል ተብሏል።
በተጨማሪም የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራትና ሌሎች ተሳታፊዎች በጉባኤዉ እና በጎንዮሽ ስብሰባዎችን እንደሚያካሂዱ ተገልጿል።
በመጨረሻም በጉባኤው የተለያዩ የዉሳኔ ሰነዶች (resolutions) ቀርበዉ ይጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ጉባኤዉ ከመጀመሩ በፊት በጄኔቫ ከተማ “ዎክ ዘቶክ!”የጎዳና ላይ ሩጫ የተካሄደ ሲሆን አትሌት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ሌሎች አትሌቶችና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል።