ቀጥታ፡

በሆርቲካልቸር ዘርፍ ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነትንና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እየተሰራ ነው---ማህበሩ


ሀዋሳ ግንቦት 13/2015(ኢዜአ)፦ በሆርቲካልቸር ዘርፍ የአገሪቱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር ገለፀ።

በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የሆርቲካልቸር መርቶች ከ550 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱም ተመላክቷል።


የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ላሉ ተማሪዎችና ለመምህራን ያዘጋጀውን የልምድ ልውውጥና የመስክ ምልከታ በባቱ ከተማ በሚገኙ የአበባ እርሻ ልማት ኩባንያዎች ውስጥ አካሂዷል።
በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት የማህበሩ የፕሮሞሽንና የኢንፎርሜሽን አገልግሎት ኃላፊ ወይዘሮ የምስራች ብርሀኑ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በተለይ በአበባ ምርትና ገበያ ከአፍሪካ ኬንያን ተከትላ በሁለተኛ፤ ከዓለም ደግሞ በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ማህበሩ ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ በአበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ዕፀ ጣዕም ምርቶች ያላትን ዓለም አቀፍ ተወዳሪነትንና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። 
ማህበሩ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያች ተወዳዳሪነታቸው አድጎ በዓለም አቀፍ ገበያ ተሳትፏቸው እንዲጨምር ብሎም አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ለማሳደግ ታልሞ መቋቋሙን አስታውሰዋል።
ማህበሩ ይህን ዓላማ ለማሳካት የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፣ በተለይ ኩባንያዎቹ በዓለም ዓቀፍ ገበያ ላይ ብቁ ሆነው እንዲቀርቡ የሚያግዙ ሥልጠናዎች መሰጠቱን ገልጸዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ ለኩባንያዎቹ የጥራት ደረጃዎችን መስጠት የሚያስችል የመመዘኛ ሥርዓት በመዘርጋት የማበረታታት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ወይዘሮ የምስራች እንዳሉት በዘርፉ ተወዳዳሪነትን ከሚጨምሩ መስፈርቶች መካከል የሥራ ላይ ደህንነትና የአመራረት ሂደት ጥራት ቁልፍ ሚና አላቸው። 
በመሆኑም ማህበሩ የተቀናጀ የተባይ ቁጥጥርና ሌሎች የምርት ጥራት አጠባበቅ ሥራዎችን ለመስራት እንዲሁም የምርት ሂደቱን ከአካባቢ ብክለት ነፃ በሆነ መንገድ ለማከናወን የሚያግዙ ሥልጠናዎችን ለኩባንያዎችና በሥራቸው ላሉ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
ማህበሩ በተለያየ መንገድ አምራችና ገዢውን የማገናኘት ሥራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊዋ፣ ዘንድሮ በስምንት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የሆርቲካልቸር መርቶች ከ550 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሰዋል። 
ከእዚህ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው የተገኘው በማህበሩ ሥር የታቀፉ አምራችና ላኪ ኩባኖያዎች ወደ ውጭ ከላኳቸው ምርቶች መሆኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይ የሆርቲካልቸር ዘርፍን በሥራ የሚቀላቀሉ ተማሪዎች የመስክ ምልከታ መሳተፋቸው በተግባር ዕውቀትና ክህሎት የበቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በሆርቲካልቸር ዘርፍ ከተሰማሩ የማህበሩ አባል ኩባንያዎች መካከል የዝዋይ ሮዝ አበባ እርሻ ልማት ኩባንያ የእርሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ተወልደ የመስክ ምልከታው ለተማሪዎች ካለው ጠቀሜታ በተጨማሪ ኩባንያዎችም በሙያው የሰለጠና ባለሙያ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል።
የሆርቲካልቸር ዘርፍ ለአገር ከሚያስገኘው ውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው ኃይል ስለሚይዝ በኢኮኖሚው ውስጥ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርትን በጥራትና ከአካባቢ ብክለት በፀዳ መልኩ ለማምረት ኩባንያቸው ትኩረት መስጠቱን የገለጹት አቶ ጸጋዬ፣ በተለይ ወደ አበባ እርሻው የሚገባው ውሃ ከእርሻው ሲወጣ አካባቢውን እንዳይበክል ፈሳሽ ተረፈ ምርትን አጣርቶ መልሶ ለግብአትነት ማዋል የሚያስችል ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ መሆኑን አስረድተዋል።
ደረቅ ተረፈ ምርትንም እንዲሁ በዘመናዊ መንገድ ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያና ባዮ ጋዝ በመቀየር ጥቅም ላይ እያዋሉ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ ከተሳተፉ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሆርቲካልቸር ትምህርት ክፍል አራተኛ ዓመት ተማሪ ህሊና ወርቁ እንዳለችው፣ የመስክ ምልከታው በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር በማየት ተጨባጭ እውቀት እንዲጨብጡ አስችሏቸዋል።
ለወደፊትም በሥራ ዓለም ላይ የሚሰጣቸውን የሥራ ሃላፊነት በብቃት መወጣት እንዲችሉ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ነው የገለጸችው።
የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር በአሁኑ ወቅት አበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና ሌሎች ምርቶችን የሚያመርቱ 120 ኩባንያዎች በሥሩ እንዳሉ ተገልጿል። 
በመስክ ጉብኝቱ ላይ የአምራችና ላኪ ማህበሩ አባል ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የሀዋሳ የኒቨርሲቲ ሆርቲካልቸር ትምህርት ክፍል መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም