ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ኮፐንሀገን ዴንማርክ አዲስ በረራ ዛሬ በይፋ አስጀመረ

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ኮፐንሀገን ዴንማርክ አዲስ በረራ ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።

በበረራው ማስጀመሪያ መረሃ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ የማኔጅመንት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ በተያያዘው የእድገት መንገድ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እያሰፋ ይገኛል ብለዋል።

ወደ ዴንማርክ የተጀመረው አዲስ በረራም ኢትዮጵያን ከዴንማርክ ብሎም ከአፍሪካ ለማስተሳሰር የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በዚህም በሀገራቱ መካከል የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ቱሪዝምን ለማሳለጥ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ ከውንስለር ሲቭ ቢያት በበኩላቸው፣ የበረራው መጀመር በዴንማርክና በኢትዮጵያ መካከል የኢኮኖሚና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ብለዋል።

እንዲሁም የሰሜንና አውሮፓ ሀገራትንና የደቡብ እስካንዲኒቪያ ሀገራትን ለማቀራረብ ሰፊ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

በረራው በሳምንት አምስት ጊዜ የሚኖር ሲሆን ኮፐንሀገን በአውሮፓ 21ኛው መዳረሻ እንደሆነች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን በፍጥነት እየጨመረ ሲሆን በዛሬው እለት ይፋ የሆነው የዴንማርክ የቀጥታ በረራ 134ተኛው አለም ዓቀፍ መዳረሻው መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም