የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማዘመን ምርትን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች ለአርሶ አደሩ በስፋት ተደራሽ ማድረግ ይገባል-የዩኒቨርሲቲ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማዘመን ምርትን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች ለአርሶ አደሩ በስፋት ተደራሽ ማድረግ ይገባል-የዩኒቨርሲቲ ምሁራን
አዲሰ አበባ ግንቦት 13/2015(ኢዜአ)፡- የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማዘመን ምርትን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶችን ለአርሶ አደሩ በስፋት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ መምህራንና ተማሪዎች በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የግብርና ሳይንስ ኢግዚቢሽን ጎብኝተዋል።
በአውደ ርዕዩ በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች፣ዲጅታላይዜሽንና የግብርና ፋይናንስ ላይ ያተኮሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡
በጎብኝቱ ላይ የተገኙ መምህራንና ተማሪዎች መንግስት ግብርናውን ለማዘመን እየሰራ ያለውን ተግባር አድንቀው ለዚህም የምሁራን ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎችም በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የግብርና ሳይንስ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ዝግጁነት መጎብኘታቸው ላቅ ያለ ትርጉም አለው ብለዋል።
በሐረማያ ዪኒቨርሲቲ የገጠር ልማት እና የግብርና ኤክስቴንሽን መምህር ቅድስና ሰብስቤ፤ ለኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ዘርፍ ማዘመንና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በመንግስት ለተጀመሩ ጥረቶች ስኬት ከምሁራን ባለፈ ሁሉም የድርሻውን ድጋፍና እገዛ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች በአውደ ርዕዩ መታደማቸው በግብርናው ዘርፍ ቀጣይ ለሚደረጉ ጥረቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊ የሚያደርጋቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማዘመን ምርትን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች ለአርሶ አደሩ በስፋት ተደራሽ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባም ገልጸዋል።
በአምቦ ዪኒቨርሲቲ የግብርና ምህድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተማራማሪ የሆኑት ብርሃኑ ከበደ፤ የኢትዮጵያ ግብርና በርካታው ህዝብ የሚተዳደርበት ቢሆንም በቴክኖሎጂ የመጠቀምና ምርትን የማሳደግ ስራ ክፍተት የሚስተዋልበት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።
በመሆኑም አሁን መንግስት የዘርፉን አስፈላጊነት በመገንዘብ በሁሉም መስክ እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በአውደ ርዕዩ ላይ የተመለከቷቸው የግብርና ሳይንስ ውጤቶች ለዘርፉ እድገት ተስፋ የሚያሳድሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ዩኒቨርሲቲዎች ለግብርና ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሊያከናውኑ ይገባልም ነው ያሉት።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ራሄል አበራ፤ በጉብኝቱ የተመለከተቻቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ትልቅ ትምህርት የቀሰመችበት መሆኑን ገልፃለች።
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው ጥረት የዩኒቨርሲቲዎች አሻራ ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የግብርና ሳይንስ ኢግዚቢሽን የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች መጎብኘታቸው ለቀጣይ ስራዎች የላቀ ትርጉም አለው ብለዋል።
በሳይንስ ሙዚየም የተሰናዳው "የግብርና ሳይንስ አውደ ርዕይ ሚያዚያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ለተመልካች ክፍት መደረጉ ይታወቃል።