52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቀቀ

368

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠናቀቀ።

በ52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፉና አሸናፊ የሆኑ ክለቦች ከዕለቱ የክብር እንግዶች ሽልማት ተቀብለዋል።

በሁለቱም ፆታዎች አጠቃላይ አሸናፊ የሆኑ ቡድኖች የዋንጫና የገንዘብ ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዳ በባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ እጅ ተረክበዋል።

እንዲሁም ለሻምፒዮናው መሳካት ሚና ለነበራቸው አካላት የምስጋና ምስክር ወረቀት ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ዮሐንስ እንግዳ እጅ ተቀብለዋል።

በእለቱ ሪከርድ ያሻሻሉ፣ 2 እና ከዛ በላይ ወርቅ ያስመዘገቡ አትሌቶችም የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

አጠቃላይ ውጤቱም፦ በሴቶች አሸናፊ፣ 1ኛ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ204 ነጥብ፣ 2ኛ መቻል በ170 ነጥብ፣ እንዲሁም 3ኛ ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በ55 ነጥብ አሸናፊ ሆነዋል።

በወንዶች አሸናፊ፣ 1ኛ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ154 ነጥብ፣ 2ኛ መቻል በ125 ነጥብ እንዲሁም 3ኛ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ 104 ነጥብ በመሰብሰብ አሸናፊ መሆናቸው ተገልጿል።

ሻምፒዮናው የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ቡድኖች እና ክለቦች በሰልፍ ትርኢት በክብር እንግዶች ፊት ያለፉ ሲሆን በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በመዘመር ተጠናቋል።

ሻምፒዮናው አጠቃላይ አሸናፊ፣ 1ኛ የኢትዮጵያ ንግደ ባንክ በ358 ነጥብ፣ 2ኛ መቻል በ295 ነጥብ እንዲሁም 3ኛ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በ158 ነጥብ አሸናፊዎች ሆነው መጠናቀቁን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም