ቀጥታ፡

ለሶስተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ተቋም ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ሊወጣ ነው- የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለሶስተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ተቋም ፈቃድ ለመስጠት በሰኔ 2015 ዓ.ም ጨረታ ሊወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር ኢንጅነር ባልቻ ሬባ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ ለሶስተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል።

ከአገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ አንዱ በመንግስት ብቻ ሲቀርብ የነበረውን የቴሌኮም አገልግሎት በማሻሻል ለአለም አቀፍ አቅራቢዎች ክፍት ማድረግ ነው።

በመሆኑም በኢትዮ ቴሌኮም ብቻ ሲሰጥ የነበረውን የቴሌኮም አገልገሎት በማስፋት ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ መንግስት ወስኗል።

በዚህም መሰረት ለሁለት አዳዲስ የቴሌኮም ተቋማት ፈቃድ ለመስጠት ቀደም ሲል ጨረታ ወጥቶ ሳፋሪኮም ኩባንያ በ2013 ዓ.ም የመጀመሪያውን ፈቃድ መውሰዱን ኢንጅነር ባልቻ ጠቅሰዋል።

በጨረታው ላይ ተሳትፎ የነበረው ኤምቲኤን ግሩፕ በወቅቱ አቅርቦት የነበረው ገንዘብ ከሳፋሪኮም አንጻር ልዩነቱ በመስፋቱ የሁለተኛው ፈቃድ ሳይሰጥ መቅረቱንም አስታውሰዋል።

በመሆኑም ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቀጥሎ ሁለተኛውን አዲስ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት በሚያወጣው የፍላጎት ፈቃድ መግለጫና ጨረታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ሲያደርግ መቆየቱን ዋና ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

የመጀመሪያውን ፈቃድ ያገኘው ሳፋሪኮም ገበያውን በውድድር ላይ የተመሰረተ ያደረገው መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያ ሶስተኛ አገልገሎት ሰጪ እንዲኖር መነሳሳት የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ባለስልጣኑ በባለድርሻ አካላት የተገኙ ግብረ መልሶችን ትንተና ጨርሶ የጊዜ መርሃ ግብር ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢንቨስተሮች አማራጮችን ተጠቅመው በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማስተዋወቅ ስራ መከናወኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ህግ መሻሻል፣ ያሉ ማበረታቻዎችና አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ፍላጎት እንዲጨምር አድርጎታል ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ለሶስተኛው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ተቋም ፈቃድ ለመስጠት በሰኔ 2015 ዓ.ም ጨረታ ሊወጣ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር ባልቻ ሬባ ገልጸዋል።

የመጀመሪያውን ፈቃድ ለመስጠት በነበረው ግልጸኝነትና የፖሊሲ አቅጣጫ በመፈጸም መንግስት ላሳየው ቁርጠኝነት ሁለት አለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘቱን አስታውሰው የቀጣዩ ጨረታም በተመሳሳይ መልኩ ይከናወናል ብለዋል።  

በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ወደ ሶሰት ማደጉ አገልግሎቱን ከማሳደግ ባለፈ የዲጂታል ሂደቱን በማፋጠን የላቀ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተመላክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም