ቀጥታ፡

በሀገራዊ ተቋማት ዙሪያ የሚሰሩ ፊልሞች ለሀገር ፍቅርና አርበኝነት እሴቶች መዳበርና ታሪክን ለመዘከር ሁነኛ አበርክቶ አላቸው--የ'ሰማዩ የኛ ነው' ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅ ይድነቃቸው ሹመቴ

 

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2015(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ተቋማት ዙሪያ የሚሰሩ ፊልሞች ለሀገር ፍቅርና አርበኝነት እሴቶች መዳበርና ታሪክን ለመዘከር ሁነኛ አበርክቶ ያላቸው መሆኑን 'ሰማዩ የኛ ነው' የተሰኘውን ዘጋቢ ፊልም ያዘጋጀው ይድነቃቸው ሹመቴ ገለጸ።

በጥንታዊቷ ባለታሪክ ኢትዮጵያ ህዝቦቿና አርበኝነት፣ ውትድርና እና ድንበር አልባዋ ኪነ-ጥበብ እርስ በርስ የተሰናሰሉ ቤተሰባውያን ናቸው።

በጥንትም ሆነ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ኪነ-ጥበብ ለኢትዮጵያውያን አርበኞች የወኔያቸው ቀለብ፣ የእምነታቸው ስንቅ፣ የጀግንነታችው ክትባት ነው።

የሀገር ህልውና ዋስትና የሆኑ የሰላምና ጸጥታ ተቋማት የኪነ-ጥበብ ሰዎች መፍለቂያ መሆናቸው፤ ኪነ ጥበብም ለተቋማቱ ክብር ስትዘክር መቆየቷ ዕሙን ነው።

ለጥቂት አስርት ዓመታት የኪነ-ጥበብና የመከላከያ ሠራዊት ቁርኝት ተቀዛቅዞ የቆየ ቢሆንም ከሰሞኑ ለዕይታ የበቁ የፊልም ጥበብ ውጤቶች ትልቅ መሻሻል ስለማሳየቱ  ሁነኛ ማሳያ መሆን ችለዋል።

በዚህም መክንያት 'ስርየት'ን ጨምሮ በተመልካቾች ሕሊና አይረሴ ፊልሞችን ለተመልካች ያደረሰው ዕውቁ የፊልም ባለሙያ ይድነቃቸው ሹመቴ፤ 'ኩራት ፒክቸርስ' በተሰኘው ድርጅቱ በኩል በታላላቅ ሀገራዊ ተቋማት ዙሪያ የፊልም ጥበብ ስራዎችን አበርክቷል።

በቅርቡ ለሀገር ደጀንና ኩራቱ የኢትዮጵያ አየር ኅይልን ቁመና የሚዳስስ 'ሰማዩ የኛ ነው' በሚል ርዕስ ለተደራሲያን ባቀረበው ዘጋቢ ፊልም፤ ከተመልካቾች ያገኘው ግብረ-መልስ 'ከጠበቅኩት በላይ ነው' ይላል።

በ'ሰማዩ የኛ ነው' ዘጋቢ ፊልም ዝግጅት ያልተለመዱ ሙያዊ ቴክኒኮችና መሳሪያዎች መጠቀሙን ገልጾ፤ በዘጋቢ ፊልሙ ስራ ሂደት የኢትዮጵያ አየር ኅይል ተልዕኮና ጀግንነት በቅርበት እንዲረዳ አስችሎታል።

ኢትዮጵያ በየጥበብ ፈርጁ ብዙ ሊባልላትና ሊተረክላት የሚችል ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ያነሳው ባለሙያው፤ እርሱ በተሰማራበት የፊልም ጥበብ በሀገራዊ ተቋማት ላይ ያተኮሩ ፊልሞቹ ፋይዳችው መልከ ብዙ ነው ይላል።

መሰል የፊልም ጥበብ ስራዎች ተቋማት ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ ከማስቻሉ ባሻገር የሀገር ፍቅርና አርበኝነት ስሜት እንዲያብብ፣ በትውልድ አዕምሮ አይረሴ ድል እና ገድል ለመተረክ ሁነኛ ሚና እንዳላችው ያነሳል።

የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት እና የኪነ-ጥበብ ድርጅቶች ተናበው በመስራት ሀገራዊ ገጽታቻውን ለመገንባት፣ ትውልዱን ወደ ተቋማቱ እንዲቀላቀል መነሳሳትና የሀገር ፍቅር በመፍጠር በቅጡ ተጠቅመውባቸዋል ይላል።

ከኢትዮጵያ አኳያ ባለሙያዎች በተናጠል ከሚያደርጓቸው ጥረቶች በስተቀር የኪነ-ጥበብ እና ወታደራዊ ተቋማት ተደጋግፈው በመስራት በኩል ውስንነቶች እንደነበሩ አስታውሷል።

አሁን አዲስ መልካም ጅምር መምጣቱን 'ሰማዩ የኛ ነው' የተሰኘው እና ከሰሞኑ ለዕይታ የሚበቃው 'ንስሮቹ' የተሰኘው ፊልምን በማሳያነት ያነሳል።

ይህም የተቋማቱን አመራሮች የሚያስመሰግን ጅማሮ አድንቆ፤ ለፊልም ኢንዱስትሪው ዕድገትም መልካም ዕድል በመሆኑ በቀጣይነት መለመድ ያለበት መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም