በዓለም አደባባይ አገርን ላስጠሩ የሲዳማ ክልል አትሌቶች እውቅናና ሽልማት ተሰጠ

315

ሀዋሳ ግንቦት 13/2015(ኢዜአ)፦ በአትሌቲክስ ስፖርት በዓለም አደባባይ አገርን ላስጠሩ የሲዳማ ክልል አትሌቶች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት እውቅናና ሽልማት የመስጠት መርሃ-ግብር ተካሄደ።

በተካሄደው መርሃ ግብር በማራቶን ውድድር ለአስር ዓመታት የዓለም ክብረ ወሰን ባስጠበቀው መቶ አለቃ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ የተጻፈ "የተፈተነ ጽናት" የተሰኘ መጽሐፍም ከ6 ሚሊዮን በሚበልጥ ገንዘብ ተሽጧል።


 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዴሞ በዚህ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት በአትሌትክሱ ዘርፍ የአገርን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ላደረጉ የክልሉ አትሌቶች የክልሉ ህዝብና መንግስት ትልቅ አክብሮት እንዳለው ገልጸዋል።

የቀደምት አትሌቶችን ጨምሮ የተሰጠው እውቅናና ሽልማት በአትሌትክሱ ዘርፍ ያለውን የክልሉን እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀምና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት መነሳሳት ለመፍጠር ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ደስታ እንዳሉት የክልሉ መንግስት በአትሌትክስ ዘርፍ ሀገርን ሊያስጠሩ የሚችሉ ወጣቶችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ ነው።

መቶ አለቃ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞን እና አትሌት ቱርቦ ቱሞን ከመሳሰሉት ስመጥር አትሌቶች ወጣቱ ትውልድ አሸናፊነትና የዓላማ ጽናት መማር እንዳለበትም ገልጸዋል።

በማራቶን የዓለም ክብረወሰን ያስመዘገበው መቶ አለቃ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞም የክልሉ መንግስት በሀዋሳ ከተማ ባዘጋጀለት 1ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አካባቢውንና ስሙን የሚያስጠራ ሥራ እንዲሰራም ጠይቀዋል።


 

የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሬው አሬራ በበኩላቸው የእውቅናና የሽልማት መርሀ-ግብሩ ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎችን ያነገበ መሆኑን ተናግረዋል።

ለክልሉ ታዋቂ አትሌቶች እውቅና መስጠት፣ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት እና የስፖርት ልማት ሥራን ማገዝ ዓላማዎቹ መሆኑንም ገልጸዋል።

በእውቅናና ሽልማት መርሀ-ግብሩ "የተፈተነ ጽናት" በሚል ርዕስ በመቶ አለቃ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ የተጻፈ መጽሐፍ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መሸጡንም ኮሚሽነር ፍሬው አስታውቀዋል።


 

የመጽሀፉ ሽያጭ ገንዝብ በቼክ፣ በጥሬ ገንዘብና ቃል በመግባት የተሰበሰበ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ለመቶ አለቃ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ ያዘጋጀውን 1ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ሳይት ፕላን አዘጋጅቶ እንደሚያስረክብም አመልክተዋል።

በህይወት ለሌለው አትሌት ቱርቦ ቱሞ ቤተሰቦችም 1 ሚሊዮን ብር፣ በዓለምና በአፍሪካ የአትሌትክስ ውድድሮች አሸናፊ ለሆኑ ሦስት ወጣት ተተኪ አትሌቶች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የ500 ሺህ ብር ሽልማት መሰጠቱን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኘው መቶ አለቃ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ ከረዥም ዓመታት በኋላ የክልሉ መንግስት ለሰጠው እውቅና አመስግኗል።

የክልሉ መንግስት በአትሌትክሱ ዘርፍ የሚያከናውነውን ተግባር በመደገፍ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እንደሚሰራም ነው ያረጋገጠው።

የአትሌት ቱርቦ ቱሞ ልጅ ወጣት መብራት ቱርቦ በበኩሏ አባቷ ከሞተ ከ14 ዓመት በኋላ የክልሉ መንግስት ለሰጠው እውቅናና ሽልማት አመስግናለች።

የቀደሞ የዘርፉን ጀግኖች መዘከርና ማስታወስ ለወጣት አትሌቶች አቅም እንደሚፈጥርም ተናግራለች።

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ሀላፊዎች፣ ባለሀብቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም