ቀጥታ፡

የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህር ዳር ከተማ ዛሬ በሊጉ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህር ዳር ከተማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃሉ።

በመርሃ ግብሩም  ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ወላይታ ድቻና የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይገናኛሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ወላይታ ድቻ በ32 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ52 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዟል።

ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በአንዱ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ባህር ዳር ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 9 ሰአት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ፊልሚያ ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ ነው።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ባህር ዳር ከተማ በ50 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና በ33 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባህር ዳር ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ተሸንፎ በሶስቱ አቻ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘ ዜና በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ ቡና ከለገጣፎ ለገዳዲ 1 ለ 1 እንዲሁም አርባ ምንጭ ከተማና አዳማ ከተማ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

የትናንት ጨዋታዎችን ተከትሎ ለገጣፎ ለገዳዲ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መውረዱ የተረጋገጠ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም