ቀጥታ፡

በባህርዳር ሲካሄድ የቆየው የአመራሮች ኮንፍረንስ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቀቀ 

 

ባህርዳር ግንቦት 12 ቀን 2015(ኢዜአ)፡-በባህር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአመራሮች ኮንፈረንስ በለውጡ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅጣጫ በማስቀመጥ ማምሻውን ተጠናቀቀ። 

"ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ህዝባችንን እናሻግራለን" በሚል መሪ ሃሳብ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ኮንፈረንሱ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ነው የተጠናቀቀው።


በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር በተሳተፉበት ኮንፈረንስ ማጠናቀቂያ በቀረበው የአቋም መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፤ በክልሉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመፈተሽ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መግባባት ላይ ተደርሷል።


 


በለውጡ የተገኙ መልካም ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል ችግሮችን እየፈተሹ በመፍታት አንድነትንና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።


በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ምክንያት የሆነውን ጽንፈኝነት በየደረጃው ያለው አመራር በጽናት በመታገል የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አቋም መወሰዱም ተገልጿል።

የአቋም መግለጫው እንዳመላከተው የማንነትና የወሰን፣ የህገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የዜጎች መብት በየትኛውም ቦታ ተከብሮ እንዲጸና፣ የተሳሳቱ ትርክቶች እንዲታረሙ የጋራ አቋም ላይ ተደርሷል።

ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ የክልሉ ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በተደራጀ አግባብ ለመከላከል መግባባት ላይ ተደርሷል።

በዚህም እስከ ታች ድረስ ያለው አመራርና አባል መላ ህዝቡን በማስተባበር ስርዓት አልበኝነትን ለመዋጋት በቁርጠኝንነት እንዲሰራ አቅጣጫ መቀመጡን በቀረበው የአቋም መግለጫ ተብራርቷል።

የክልል ህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በኢትዮጵያ ጥላ ስር መሆኑን በኮንፈረንሱ በተደረገ ውይይት መተማመን ላይ ተደርሷል።

ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ችግሩን በመገንዘብ ትብብሩንና ድጋፉን እንዲያሳይ በኮንፈረንሱ በወጣው የአቋም መግለጫ ጥሪ ቀርቧል።


በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም