ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ሦስት ዓመታት ፈተናዎችን ተቋቁሞ በአማካይ 6 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል- የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ

አዲስ አበባ ግንቦት 12/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተተገበረው የመጀመሪያው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፈተናዎችን ተቋቁሞ በአማካይ 6 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ። 

ከ2016 እስከ 2018 የሚተገበር የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛ ምዕራፍ ዕቅድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

የ2015 በጀት ዓመት የመንግስት የዘጠኝ ወራትና የሦስተኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ሚኒስትሮች በተገኙበት ተካሂዷል።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በዚሁ ወቅት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የመጀመሪያ ምዕራፍ አፈጻጸምና የሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ዝግጅትን  በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ሶስተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗ፣ የህዝብ ብዛቷ፣ ቀጣይነት እና ብዝሃነት ያለው ኢኮኖሚ መገንባቷ ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

መንግስት ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀዳውን የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት በመተግበር ስኬት ማስመዝገቡን አንስተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተፈጥራዊ እና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች ውስጥም ሆኖ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ካስመዘገቡት አማካኝ የ3 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ሲነጻጸር በእጥፍ ማደጉን ገልጸዋል።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በኮቪድ 19፣ በግጭት፣ በድርቅና ጦርነት፣ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት እና በልማት አጋሮች ድጋፍ ማቋረጥ ትላልቅ ተግዳሮቶች  ተፈትኖ እንደነበር አንስተዋል።

ሆኖም መንግስት በወሰዳቸው ቁልፍ እርምጃዎችና የራስን አቅም አሟጦ መጠቀም ላይ ባተኮሩ ተግባራት ኢኮኖሚው ባለፉት ሦስት ዓመታት በአማካይ የ6 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

በተለይም በግብርናው፣ በአገልግሎት እና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በብዙ መልኩ እመርታዎች መምጣታቸውን አብራርተዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ መጠናቀቁን ተከትሎም  ከ2016 እስከ 2018 የሚተገበር ሁለተኛ ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ መዘጋጀቱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በዚህኛው ምዕራፍ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ አካባቢ መፍጠር፣ የዘርፎችን የማምረት አቅምና ምርታማነት ማስፋት እና የመንግስትን የመፈጸም አቅም ማጎልበት ላይ ያተኮሩ አራት ቁልፍ ምሰሶዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግርን ማፋጠን፣ ኢንቨስመንት እና ቁጠባን ማሳደግ፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ትኩረት እንደሚሰጣቸው አንስተዋል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የተረጋጋ የገበያ ስርዓት መፍጠር፣ የመንግስት በጀት ጉድለትን ጤናማነት ማስተካከል እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን የማሻሻል ግብ መያዙን አብራርተዋል።

የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን ለመገንባት የተሻለ ሀብት አሰባሰብ፣ የመንግስት ወጭ ቅነሳ እና የዕዳ አስተዳደር እንዲሁም የፋይናንስ ተደራሽነት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል። 

ምቹ ኢንቨስትመንትና የንግድ አካባቢን ለመፍጠርም የገበያ ተደራሽነትንና ተወዳዳሪነትን ማሻሻል፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ማነቃቃት፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን መጨመር እና ጥራትን ማረጋገጥ ላይ እንደሚሰራ ነው ያብራሩት።

የዘርፎችን የማምረት አቅምና ምርታማነትን  ለማስፋትም የወጪ ንግድን ማሳደግ፣ ሀገራዊ ገጽታና ቱሪስት መዳረሻ ልማት እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ጨምሮ ሰፋፊ ግቦች መያዛቸውን ገልጸዋል።

የመንግስትን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ደግሞ ብቁ፣ ውጤታማና የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት መፍጠርና ብልሹ አሰራርን ማስወገድ እንዲሁም ዘመናዊ አሰራርን የመከተል ግቦች አሉ ብለዋል።

ለሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምዕራፍ ስኬት በልማት ፋይናንስ፣ በኢንቨስትመንት፣ በገበያ ማስፋት፣ ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ዙሪያ ቅንጅታዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የተያዘው ሀገራዊ ግብ እንዲሳካ ቁልፍ ሚና ያለው ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀዳሚው ስራ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም