የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የጎንደር ዲስትሪክት በመሰረተ ልማት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመግታት የህብረተሰቡን ትብብር ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የጎንደር ዲስትሪክት በመሰረተ ልማት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመግታት የህብረተሰቡን ትብብር ጠየቀ
ጎንደር ግንቦት 12/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የጎንደር ዲስትሪክት በአካባቢው የኤሌትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመግታት የህብረተሰቡን ትብብር ጠየቀ።
ዲስትሪክቱ በጎንደር ከተማ በኤሌትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከተገልጋይ ደንበኞቹ ጋር የውይይት መድረክ ዛሬ አካሂዷል፡፡
የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ አበራ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በመሰረተ ልማቱ ላይ በየጊዜው እየደረሰ ያለው ዝርፊያና ውድመት ዲስትሪክቱ ለደንበኞቹ የተሟላ የኤሌትሪክ አገልግሎት እንዳያቀርብ ችግር ፈጥሮበታል፡፡
ባላፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ዲስትሪክቱ በሚያስተዳድራቸው ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን በምእራብና በማእከላዊ ጎንደር ዞኖች ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኤሌትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ዝርፊያና ጉዳት መድረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በአካባቢው በከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ የብረት ምሰሶዎች፣ የእንጨትና የኮንክሪት ፖሎች እንዲሁም በመካከለኛና ከፍተኛ ትራንስፎርመሮች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
በዚህ የንብረት ዝርፊያና ውድመቱ ምክንያት በደንበኞች ዘንድ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የመሰረተ ልማት ዝርፊያው ዲስትሪክቱ ከሚሰጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሰብሰብ የሚገባውን ገቢ እያሳጣው መሆኑን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ አጥፊዎችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት ረገድ የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
ተቋሙ ከህግ አካላት ጋር በመቀናጀት ጉዳት አድራሽ ግሰለቦችን ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብ በተደረገ ጥረትም 16 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንዲመሰረትባቸው መድረጉን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኤሌትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ዝርፊያና ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።
ዲስትሪክቱ የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የደንበኞቹን እርካታ ለማረጋገጥ ከመጪው ሃምሌ ወር ጀምሮ ዲጂታል የክፍያ ስርአት ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁንም ገልፀዋል፡፡
በፍጆታ ሂሳብ ላይ በደንበኞች የሚቀርበውን ቅሬታ ለመፍታትና የመብራት መቆራረጥንና መጥፋትን ክትትል ለማድረግ የሚያስችል ለከፍተኛ የሃይል ተጠቃሚዎች የ'ስማርት' ቆጣሪ አገልግሎት መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡
ከውይይት ተሳታፊዎች መካከል በጎንደር ከተማ የሮዚዮ ሆቴል ባለቤት ወይዘሮ አምሳል ጌታለም፣ ''ችግሩ ሁሉንም እየጎዳ በመሆኑ አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብ ግዴታ አለብን'' ብለዋል።
''የመብራት በተደጋጋሚ መቋረጥ ደንበኞችን ለማስተናገድም ሆነ ሰርቶ ለመንግስት ግብር ለመክፈል አስቸጋሪ በመሆኑ በመሰረተ ልማቱ የሚደርሰውን ጉዳት በጋራ ልንከላከለው ይገባል'' ነው ያሉት፡፡
በምእራብ ጎንደር ዞን የአብርሃጅራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ አለሙ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በተደጋጋሚ የመብራት መቋረጥ ለታማሚዎች የተሟላ ህክምና ለመስጠት እንደተቸገረ ተናግረዋል፡፡
በኤሌትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በሚፈፀም ዝርፊያ የሚፈጠረው የመብራት መቋረጥ በህክምና ተቋማት የሰው ሕይወት እንዲጠፋ የሚያደርግ በመሆኑ ''ተጋግዘን አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብ ይገባናል'' ብለዋል፡፡
ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ በማእከላዊና በምእራብ ጎንደር ዞኖች 25 የአገልግሎት መስጫ ማእከላት ያሉት ዲስትሪክቱ በአሁኑ ወቅት ከ109 ሺህ በላይ የኤሌትሪክ ደንበኞች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡