በኢትዮጵያ የኢኮኖሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ገበያ መር የሰው ኃይልና የክህሎት ልማት ሪፎርም ተደርጓል -የስራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ገበያ መር የሰው ኃይልና የክህሎት ልማት ሪፎርም ተደርጓል -የስራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ግንቦት 12/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኢኮኖሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ገበያ መር የሰው ኃይልና የክህሎት ልማት ሪፎርም በማድረግ ውጤታማ ስራ መከናወኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በበኩላቸው፤ በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፌደራል መንግስት ተቋማት የዘጠኝ ወር የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተገምግሟል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሰው ኃይል እና የክህሎት ልማት ሥራ ገበያ መር እንዲሆን የሚያስችል ሪፎርም ተደርጓል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ100 በላይ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መንገድ የክህሎት ስልጠና እንዲሰጡ በማደራጀት የለውጡን እሳቤዎች ገቢራዊ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
የክህሎት ስልጠናው የገበያውንና የኢኮኖሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በዚህም በዘጠኝ ወራት ብቻ ለሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በቀጣይም የፋይናንስ አቅርቦት፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎችን በተመለከተ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሁም ኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፎች እመርታ እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብዙ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል አሰራር እየገቡ በመሆናቸው፤ በዚህም የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት በዲጂታል ኢኮኖሚ ውጤት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል፡፡
የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ መገምገሙን አንስተዋል፡፡
በኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፍም የሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ስራዎችን የሚያቀላጥፉ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች እንዲዘጋጁ በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡