የደን ልማቱ ዘላቂ እንዲሆን በጥናትና ምርምር የተረጋገጠ የአገር በቀል ዛፍ ዝርያዎችን የማሰባሰብና የማከፋፈል ስራ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ደን ልማት - ኢዜአ አማርኛ
የደን ልማቱ ዘላቂ እንዲሆን በጥናትና ምርምር የተረጋገጠ የአገር በቀል ዛፍ ዝርያዎችን የማሰባሰብና የማከፋፈል ስራ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ደን ልማት
ሀዋሳ ግንቦት 12 / 2015 (ኢዜአ) የደን ልማቱ ዘላቂ እንዲሆን በጥናትና ምርምር የተረጋገጠ የአገር በቀል ዛፍ ዝርያዎችን የማሰባሰብና የማከፋፈል ስራ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት የሀዋሳ ዋና ማዕከል አስታወቀ።
የማእከሉ ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ ብሩክ ብርሃን ለኢዜአ እንዳሉት ማእከሉ በዋናነት በደቡብ ኢትዮጵያ በተመረጡ አካባቢዎች በደን ጥበቃና ምርምር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።
ዋና ዓላማው የሀገሪቱ የደን ሽፋን እንዲያድግ የዛፍ ዝርያዎችንና የሚተከሉበትን አካባቢ ልየታ ማካሄድ፣ ጥራት ያላቸው ችግኞችን በድጋፍ መልክ በማፍላት ለማህበረሰቡ ማቅረብ እንዲሁም በምርምር የተደገፈ የደን ልማት በየደረጃው እንዲካሄድ የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት ነው ብለዋል።
ማእከሉ በሁለት መንገዶች የዛፍ ዝርያዎች እንደሚሰበስብ አመልክተው፣ አንደኛው ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በራሱ ይዞታ ከችግኝ ደረጃ አንስቶ በመንከባከብና በመጠበቅ ለዘር ምርት ማብቃት መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው ደግሞ በቀጥታ በጫካ ውስጥ ተገብቶ የግንድና የቅርንጫፍ ሁኔታቸው ጥሩ የሆኑ የዛፍ ዓይነቶች ሲገኙ የተፈጥሮ ደን ውስጥ በመከለልና በመጠበቅ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ዘር በጥንቃቄ በመሰብሰብ ወደ ኢትዮጵያ ደን ልማት መላክ ነው ብለዋል።
በይርጋለም የዛፍ ዘር ምንጭና የደን ምርምር ሙከራ ጣቢያ ስር የሚገኘው 50 ሄክታር ጥብቅ ደን የዛፍ ዘር ምንጭ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን አስረድተዋል።
በይርጋለም ጥብቅ ተፈጥሮ ደን ውስጥ ከሚገኙ ነባር አገር በቀል ዛፍ ግንድ ላይ ውይም 'እናት ዛፍ' ዘር በመውሰድ በጥናትና ምርምር አረጋግጦ የማሰበሰብና ማከፋፈል ስራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ከይርጋለም በተጨማሪ በወላይታና ጋሞ ዞኖች በተመረጡ የዛፍ ዘር ምንጭ ሳይቶችም የሞሪንጋ ወይም ሽፈራው፣ የግራር፣ የባህር ዛፍ፣ የዝግባ፣ ፅድና ከመሳሰሉት 'እናት ዘርን' ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዛፍ ዘር አብዛኛውን ጊዜ በዓመት አንድ ጊዜ እንደሚሰበሰብ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣ በዚህም የችግኝ ዝግጅት ወቅትን ባገናዘበ መልኩ ተፈፃሚ እንደሚሆን አብራርተዋል።
ጥራት ያለው የዛፍ ዘር መጠቀም ያልተጣመመ፣ ጠንካራ፣ በሽታዎችንና ተባዮችን የሚቋቋም እንዲሁም ከአካባቢው ስነ-ምህዳር ጋር ተላምዶ ቶሎ የሚጸድቅ ችግኝ ያስገኛል ብለዋል።
በመሆኑም ማእከሉ ጥራት ያላቸው የእናት ዛፍ ዘሮችን በመሰብሰብና ወደ ዋናው ማእከል በመላክ የደን ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በምርምር የተደገፈ የደን ልማት እንዲካሄድ ማእከሉ ጥራት ያላቸው ችግኞች በድጋፍ መልክ በማፍላት ለአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር ያቀርባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ባለፈው ዓመት ብቻ በምርምር የተረጋገጠና በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀ 60 ሺህ ችግኞች በማፍላት በስልጤ ዞን ሁልባረግ ወረዳ ማሰራጨቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ደን ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና ማህበራዊ ረገድ የሚያስገኘው ጥቅም የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ ማእከሉ ማህበረሰቡ የደን ሀብቶችን በባለቤትነት መንፈስ እየተንከባከበ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ተመቻችቷል ብለዋል።
በይርጋለም ከተማ የአዋዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ቀለሟ ሀብተማርያም በሰጡት አስተያየት በማእከሉ የይርጋለም የዛፍ ዘር ምንጭና የደን ምርምር ሙከራ ጣቢያ እሳቸውንና የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።
ከጣቢያው በየቀኑ የግጦሽ ሣር በማጨድና ላሞቻቸውን በመቀለብ ከወተት ሽያጭ በሚያገኙ ገቢ ተጠቃሚ መሆናቸውንና ጥብቅ ደኑ የኑሮአቸው ዋስትና በመሆኑ ከአካባቢያቸው ማህበረሰብ ጋር ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርጉለት ተናግረዋል።
በጣቢያው በጥበቃ ሰራተኛነት የሚያገለግሉት አቶ በየነ ኮዬሶ የአካባቢው ማህበረሰብ ደኑን በባለቤትነት መንፈስ ስለሚመለከተውና በተቀናጀ መንገድ ስለሚጠብቀው ከጭፍጨፋ ታድጎታል ብለዋል።