ቀጥታ፡

በኢትዮ-ኢንተርናሽናል ንግድ ትርኢት እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል-የንግድ ትርኢቱ አስተባባሪ

አዲስ አበባ  ግንቦት 12/2015 (ኢዜአ) በኢትዮ-ኢንተርናሽናል 2023 የንግድ ትርኢት በግብርናው ዘርፍ  እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የገበያ ትስስር  መፈጠሩን የንግድ ትርኢቱ አስተባባሪ  ኢንጂነር ሰመኻር ተስፋዬ ገለጹ።

ለሀገር ውስጥ አምራቾች ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስርን መፍጠር ዓላማ ያደረገው ኢትዮ-ኢንተርናሽናል ኤክስፖ ከግንቦት 9 እስከ 11/2015 ዓ.ም ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በበይነመረብ አማካይነት በኦን ላይን እና በአካል በተካሄደው የንግድ ትርኢት በግብርና፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በታዳሽ ኃይልና ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እንዲሁም ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ አምራቾች ለዓለም አቀፍና ሀገር ወስጥ ሸማቾች ምርታቸውን ማቅረባቸው ተነግሯል።

በንግድ ትርኢቱ የቅባት እህሎችን በማቅረብ ከሶማሌላንድ ከመጣ የንግድ ተቋም ጋር ሲገበያይ ያገኘነው ሀብታሙ አረጋዊ እንደዚህ አይነት መድረኮች ለሀገር ውስጥ አምራቾች በርካታ ጠቀሜታ ይዘው እንደሚመጡ ገልጿል።

መድረኩ ከዓለም አቀፍ ሸማቾች ጋር በሚፈጥረው ትስስር የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብና የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት እድል እንደሚፈጥርም ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ምርቶችን በሶማሌላንድ ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከሶማሌላንድ የመጡት መሀመድ ዑስማን ናቸው።


 

እንደዚህ ዓይነት መድረኮች የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ተደራሽነት በማስፋት የሀገራቱንም ግንኙነት እንደሚያልቅ ነው አስተያየት ሰጪው ገለጹት።

የኢትዮ ኢንተርናሽናል ኤክስፖ አስተባባሪ ኢንጂነር ሰመኻር ተስፋዬ የንግድ ትርኢቱ ዋና ዓላማ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ከዓለም አቀፍ ሸማቾች ጋር ማስተሳሰር መሆኑን ገልጸዋል።

በንግድ ትርዒቱ የገበያ ትስስር ከተፈጠረላቸው መካከል በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ተሳታፊዎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

የግብርናው አምራቾች ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ አሜሪካና ሌሎች ሀገራት ከመጡ ዓለም አቀፍ ሸማቾች ጋር ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የንግድ ትስስር እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

አምራቾች ከሀገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፍ ሸማቾች ጋር የሚኖራቸውን የገበያ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችሉ የመሰረተ ልማትና ሌሎች ድጋፎች መደረግ እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

በኢትዮጵያና አሜሪካ በአካል እንዲሁም በኦን ላይን በተካሄደው ኢትዮ-ኢንተርናሽናል ንግድ ትርኢት 375 ድርጅቶች መሳተፋቸውን ከመርሐ ግበሩ አዘጋጆች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም