ቀጥታ፡

52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ፍጻሜውን ያገኛል

አዲስ አበባ ግንቦት 12/2015 (ኢዜአ):- 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ይጠናቀቃል።

ሻምፒዮናው ከግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በውድድሩ ላይ በወንዶች 743 በሴቶች 527 በድምሩ 1 ሺህ 270 አትሌቶች ተሳታፊ እንደሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

አትሌቶቹ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦችና የተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ መሆናቸውን ገልጿል።

የሻምፒዮናው አላማ በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም በሀንጋሪ ቡዳፔስት ለሚካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች አቋማቸውን እንዲለኩና በክልሎች፣ከተማ አስተዳድሮች፣ ክለቦችና በማሰልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል መፍጠር እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት መሆኑ ተመላክቷል።


 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከ2 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር በላይ በጀት መመደቡን ጠቁሟል።

ከዚህ ውስጥ 541 ሺህ ብሩ ለተወዳዳሪዎች የሚበረከት የገንዘብ ሽልማት መሆኑን ነው ያስታወቀው።

በሻምፒዮናው ዛሬና ነገ የተለያዩ የማጣሪያንና የፍጻሜ ውድድሮች ይደረጋሉ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኝ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም