ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ 

 

አዲስ አበባ ግንቦት 12/ 2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት አዳማ ከተማ ከአርባ ምንጭ ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አዳማ ከተማ በ32 ነጥብ 8ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን አርባ ምንጭ ከተማ በ25 ነጥብ 14ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

አዳማ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ አንዱን ተሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 

ተጋጣሚው አርባ ምንጭ ከተማ  በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

አንድ ጊዜ ተሸንፏል አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ አርባ ምንጭ ከተማ  1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ሁለተኛው የ25ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና ለገጣፎ ለገዳዲ መካከል ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ይደረጋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ኢትዮጵያ ቡና በ34 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ለገጣፎ ለገዳዲ በ11 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ ሽንፈት አስተናግዷል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ለገጣፎ ለገዳዲ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። በአራቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ቡና ለገጣፎ ለገዳዲን አሸንፎ አርባ ምንጭ ከተማ አዳማ ከተማን ቢያሸንፍ ለገጣፎ ለገዳዲ አምስት ጨዋታ እየቀረ ከፕሪሚየር ሊጉ የሚወርድ የመጀመሪያው ክለብ ይሆናል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሐግብር እስከ ግንቦት 15/2015 ድረስ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም