ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዓለም አቀፍ የብቃት ምዘናን አለፈ


አዲስ አበባ ግንቦት 12/ 2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በዓለም አቀፍ የብቃት አረጋጋጭ ተቋም የተደረገለትን ፍተሻ ማሟላት መቻሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ለሚገኙ ቤተ ሙከራዎች ኢንዱስትሪዎች አክሪዲቴሽን፣ የምዘና እና የኢንስፔክሽን አገልግሎት ለሚሰጠው ተቋም ምዘናውን ያካሄደው የአፍሪካ አክሪዲቴሽን ትብብር/AFRAC/ መሆኑን ገልጿል። 

አገልግሎቱ በምዘናው የአክሪዲቴሽን ሰርተፍኬት ባለቤት መሆኑ ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ‘IAF’ እና ‘ILAC’ የተሰኙ ዓለም አቀፍ እውቅናና ብቃት ማረጋጋጫ ተቋማት የሚሰጡት ሰርተፍኬት ባለቤት እንደሚያደርገው ተጠቁሟል።

ይህም ጥራታቸው በአገር ውስጥ ተመርምሮ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችና አገልግሎቶች ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድግ ተመላክቷል።


የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት ታዬ የተቋሙን አገልግሎት ማስፋትና ማሳደግ ላይ በትኩረት በመሰራቱ ለተገኘው ውጤት መብቃት መቻሉን አመልክተዋል።


ተቋሙ በቀጣይም የተሻለ በመስራት የተሰጠውን እውቅና ማስቀጠል እንደሚገባው ማሳሰባቸውን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም