የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ከአሜሪካን የግምጃ ቤት ምክትል ረዳት ፀሀፊ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ከአሜሪካን የግምጃ ቤት ምክትል ረዳት ፀሀፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015(ኢዜአ)፦የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የአሜሪካን የግምጃ ቤት ምክትል ረዳት ፀሀፊ ከሆኑት ኤሪክ ሚየር ጋር ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ወቅትም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ፣ ስለሽግግር ፍትህ እንዲሁም በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለምክትል ረዳት ፀሃፊው ገለፃ አድርገውላቸዋል ።
የአገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ እና እየታየበት ያለውን እመርታ በሚመለከት ሚኒስትር ዴኤታው ዝርዝር መረጃ የሰጡ ሲሆን ፖሊሲው አገሪቱ ከባድ ችግር አጋጥሟት እንኳ የተሻለ ኢኮኖሚ እንዲኖራት ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአመት በፊት ከአጎዋ የቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል ተጠቃሚነት እንድትወጣ መደረጉ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደር ምስጋኑ ፤ዳግም ወደ ተጠቃሚነት እንድትመለስ ግምጃ ቤቱ የድርሻውን እዲወጣ ጠይቀዋል።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የወደሙ ንብረቶችን መልሶ ለመጠገንና ዜጎችን ለማቋቋም በሚደረገው ሂደት ኢትዮጵያ የአሜሪካንን ድጋፍ አጥብቃ እንደምትሻም ሚኒስትር ዴኤታው ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
ኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተሰሩ በሚገኙ ስራዎች ዙሪያም ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ አድርገዋል።
ምክትል ረዳት ፀሀፊው ኤሪክ ሚየር በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና አሜሪካን ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል በኢትዮጵያ በኩል እየተሰራ ያለውን በጎ ስራ ያደነቁ፥ ሲሆን አገራቸው ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ኤሪክ ሚየር የኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መጠናከር ቀጠናውን ጭምር የሚያሳድግ በመሆኑ መንግስታቸውም ሆነ ተቋማቸው ይሄን ከግምት ያስገባ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል ።