ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሴቶች የሃብት ባለቤትነትና የውሳኔ ሰጭነት ሚና መሻሻል ማሳየቱን አንድ ጥናት አመለከተ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የሴቶች የሃብት ባለቤትነትና የውሳኔ ሰጭነት ሚና መሻሻል ማሳየቱን አንድ ጥናት አመለከተ።

ጉዳዩን በማስመልከት በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ ጥናት አካሂደዋል።

የጥናቱን አጠቃላይ ሂደትና ውጤቱን በሚመለከትም በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሶርሴ ጉተማ ገለጻ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም ለጥናቱ 996 አካባቢዎች ተለይተው 28 ሺህ ሰዎች ለናሙናነት የተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥናቱ እ.ኤ.አ በ2022 ሲካሄድ በትግራይ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች በነበሩ ወቅታዊ ችግሮች የጥናት ናሙናዎች አለመወሰዳቸውንም ጠቅሰዋል።

ጥናቱ የተከናወነው በሴቶችና በወንዶች መካከል የውሳኔ ሰጭነት ሚና እና የሃብት ባለቤትነት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ መሆኑንም ወይዘሮ ሶርሴ አስረድተዋል።

በጥናቱ ግኝት መሰረትም ሴቶች በቤተሰብ አስተዳደር፣ በፋይናንስ፣ በገጠርና የከተማ የመሬትና የቤት ባለቤትነት እና በሌሎችም የሴቶች ተሳትፎና ውሳኔ ሰጭነት እየተሻሻለ መምጣቱ ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ የሴቶች የሃብት ባለቤትነትና የውሳኔ ሰጭነት ሚና መሻሻሎች ቢኖሩትም ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር በቀጣይ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ጥናቱ ያሳያል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ፤ የጥናቱ መከናወን የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጉላት መንግስት እያከናወነ ለሚገኘው ጥረት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

የድህነትና የችግር ተጋላጭነት ምጣኔን ለመቀነስና የዜጎችን የአኗኗርና የሃብት ባለቤትነት ሁኔታ ለመረዳትም የላቀ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ፤ በጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ ለአገር እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ጥናቱ በተለይም የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማጎልበት እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በመሆኑም የጥናት ግኝቱን ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ በማድረግ እንዲሰሩበት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም