ቀጥታ፡

ፌዴራል ፖሊስን መቀላቀላችን ለላቀ አገራዊ ሃላፊነትና የህዝብ አገልግሎት እንድንዘጋጅ አድርጎናል-የቀድሞ ልዩ ሃይል አባላት

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015(ኢዜአ)፦ ፌዴራል ፖሊስን መቀላቀላችን ለላቀ አገራዊ ሃላፊነትና የህዝብ አገልግሎት እንድንዘጋጅ አድርጎናል ሲሉ የቀድሞ የክልሎች ልዩ ሃይል አባላት ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ወደ ፌደራል ፖሊስ ለተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ሀይል አባላት የአቀባበል እና የስልጠና መርሃ ግብርን አስጀምረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጠንካራና የተደራጀ የፖሊስና የመከላከያ ኃይል ለመገንባት በክልሎች የነበሩ ልዩ ሃይሎችን በመረጡት ሃይል ውስጥ እንዲቀላቀሉ በመንግስት ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።

በዚሁ ውሳኔ መሰረት ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ፌደራል ፖሊስን በመምረጥ በርካታ የቀድሞ የክልል ልዩ ሃይል አባላት ወደ ፌደራል ፖሊስ ተቀላቅለዋል፡፡
 

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ወደ ስልጠና ለመግባት አቀባበል ከተደረገላቸው መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ከድር መሃመድ እና አበባው ታደለ በሰጡት አስተያየት የፌዴራል ፖሊስን በመቀላቀላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው በሚኖራቸው የስልጠና ጊዜ ጥሩ የሙያ ክህሎት እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

የፌዴራል ፖሊስን መቀላቀላችው ለላቀ አገራዊ ሃላፊነትና የህዝብ አገልግሎት እንዲዘጋጁ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ወደ ፌደራል ፖሊስ የተቀላቀሉት ብሩክ ንጉሴ እና ዋልቴ ካሳሁን በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በክልል ደረጃ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ደግሞ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ አደረጃጀት ባለው ፌዴራል ፖሊስ አገራዊ ተልእኮዎችን ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በሙያቸው ዜጎችን በታማኝነት፣ በእኩልነት እና ፖሊሳዊ ስነ-ምግባርን አክብረው የሚሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የፖሊስ ዶክትሪን፣ ፖሊሳዊ ስነ-ምግባር፣ ወንጀል መከላከልና በሌሎችም ስልጠና የሚወስዱ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም