ቀጥታ፡

አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአራት ክልሎችና አንድ ከተማ አስተዳደር የተሳታፊዎች ልየታ እንደሚጀምር ገለጸ

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በጋምቤላ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦችና በሀረሪ  ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተሳታፊዎችን ልየታ ስራን እንደሚጀምር ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ በአራት ክልሎችና አንድ ከተማ አስተዳደር የሚጀምረውን የተሳታፊዎች ልየታ ስራን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በመግለጫቸው፤ በቀጣይ ሳምንት የዝግጅት ምዕራፉን በማጠናቀቅ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ሽግግር ይደረጋል ብለዋል። 

በዚህም በጋምቤላ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ በሀረሪ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተሳታፊዎች ልየታ ስራ በይፋ እንደሚጀመርም ገልጸዋል፡፡

የልየታ ስራው በወረዳዎች 'ልዩ ወረዳዎች' ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጀመር ገልጸዋል ።

ኮሚሽነሩ ተወካዮችን በወረዳዎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማስመረጥ ያስፈለገው በአንድ ጊዜና በቀጥታ ሁሉንም ዜጎች ማሳተፍ አዳጋች በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ 

በመሆኑም የተሳታፊዎች ልየታ በወረዳዎች ውስጥ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳባችንን ያሰሙልናል የሚሏቸውን ሰዎች እንዲወክሉ በማድረግ እንዲሳተፉ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለ አገር በሚደረገው ምክክር በወከሏቸው ተወካዮች አማካኝነት ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል፡፡  

በወረዳ የተለዩት ተወካዮች በክልሎች ከተወከሉ የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ጋር አጀንዳ በማሰባሰብ ተግባር እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በፌደራል ደረጃ የሚወከሉ ባለድርሻ አካላት በተወካዮቻቸው አማካኝነት አጀንዳ በማሰባሰብ ተግባር እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በወረዳ ደረጃ ሴቶች፣ እድሮች፣ ወጣቶች የማህበረሰብ መሪዎች የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብ እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን  ጠቁመዋል፡፡ 

እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች በኮሚሽኑ ጠያቂነት እያንዳንዳቸው 50 ሰዎችን ከየወረዳዎቻቸው ወክለው የሚልኩ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከነዚህ መካከል በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለሚደረጉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችን መርጠው ወደ ክልል እንደሚልኩ አመላክተዋል፡፡
 

ምክትል ኮሚሽነር ሒሩት ገብረስላሴ በበኩላቸው አገራዊ የምክክር መድረኩን ሒደት ይበልጥ አሳታፊና አካታች ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ 

የተሳታፊዎች ልየታ ተግባር ሲከናወን ሙሉ ሒደቱን የሚመራውና የሚከታተለው ኮሚሽኑ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የኢትዮጵያ አገር አቀፍ እድሮች ማህበራት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞችንና የወረዳ ተወካዮችን በተባባሪነት ለይቷል፡፡

እነዚህ አካላት የሒደቱን አካታችነት፣ ግልጽነት፣ አሳታፊነት እና ተዓማኒነት በመታዘብ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ ይሆናል፡፡

የልየታ ሂደቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በተቀሩት ክልሎች በቅርቡ እንደሚካሄድ ኮሚሽኑ በመግለጫው አሳውቋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም