የገበያ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉና ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን በማፍለቅ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገበያ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉና ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን በማፍለቅ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እየተሰራ ነው
ሐረር ግንቦት 11/2015 (ኢዜአ) ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ከማፍራት ጎን ለጎን የገበያ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉና ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን በማፍለቅ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን የሐረሪ ክልል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ አስታወቀ ፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጃፈር ሱፊያን በክልሉ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ የተዘጋጀን የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ዛሬ ከፍተዋል፡፡
የኮሌጁ ዲን አቶ ሚልኬሳ አህመድ በበኩላቸው ኮሌጁ ብቁ ተወዳዳሪና የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ሙያተኞችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"በዚህም የገበያ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉና ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን በማፍለቅ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እየተሰራ ነው" ብለዋል።
በኮሌጁ የሚመረቱ የፈጠራ ውጤቶች ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በኤግዚቢሽኑ ላይ የቀረቡና በኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች የተሰሩ የማተሚያ መሣሪያዎች፣ ዘመናዊ የንብ ቀፎ፣ የበቆሎ መፈልፈያ፣ የጨርቃ ጨርቅና ሌሎች የፈጠራ ውጤቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል ።
በቀጣይም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በብዛት በማምረት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጃፈር ሱፊያን በኤግዚቢሽኑ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት "ኮሌጁ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል፡፡
ኮሌጁ ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራትና ገበያው የሚፈልጋቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በማምረት እረገድ የጀመረውን ጥረት በማጠናከር የተቋቋመለትን አላማ እንዲያሳካ አስገንዝበዋል፡፡
በኮሌጁ የጨርቃጨርቅ ትምህርት ዘርፍ አሰልጣኝ መምህር ሄኖክ ሰይፉ በሰጡት አስተያየት በኤግዚቢሽኑ በአንድ ጊዜ አራት የህትመት ሥራዎችን የሚያከናውን የማተሚያ መሣሪያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
ማተሚያው በ26 ሺህ ብር ወጪ የተመረተ መሆኑን ጠቁመው ከውጭ የሚገቡ ማተሚያዎችን ለመተካት እንደሚያስችልና በተለይ ለኢንተርፕራይዞች ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣይ ማተሚያውን በብዛት አምርቶ ለማሰራጨት ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል።
በኤግዚቢሽኑ ላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ይዘው ያቀረቡት የእንጨት ሥራ አሰልጣኝ መምህር ኤርሚያስ መስፍን በበኩላቸው በአንድ ጊዜ እስከ 140 ኪሎ ግራም ማር የሚይዝና ዝናብ የማያስገባ የንብ ቀፎ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ቀፎው ለነፍሳትና ለተሳቢ እንስሳት ያለው ተጋላጭነትን የቀነሰ መሆኑንና በ5 ሺ 700 ብር ወጪ እንደተመረተም አስረድተዋል፡፡